ኦሪት ዘፍጥረት. Chapter 32
1 ፤ ያዕቆብም መንገዱን ሄደ፥ የእግዚአብሔር መላእክትም ተገናኙት።
2 ፤ ያዕቆብም ባያቸው ጊዜ። እነዚህ የእግዚአብሔር ሠራዊት ናቸው አለ፤ የዚያንም ስፍራ ስም መሃናይም ብሎ ጠራው።
3 ፤ ያዕቆብም ወደ ወንድሙ ወደ ዔሳው ወደ ሴይር ምድር ወደ ኤዶም አገር ከፊቱ መልእክተኞችን ላከ፤
4 ፤ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው። ለጌታዬ ለዔሳው። ባሪያህ ያዕቆብ እንዲህ አለ ብላችሁ ንገሩት። በላባ ዘንድ በስደት ተቀመጥሁ፤ እስከ አሁን ድረስ ቆየሁ፤
5 ፤ ላሞችንም አህዮችንም በጎችን ወንዶች ባሪያዎችንም ሴቶች ባሪያዎችንም አገኘሁ፤ አሁንም በፊትህ ሞገስን አገኝ ዘንድ ለጌታዬ ለማስታወቅ ላክሁ።
6 ፤ መልእክተኞቹም ወደ ያዕቆብ ተመልሰው እንዲህ አሉት። ወደ ወንድምህ ወደ ዔሳው ሄደን ነበር፤ እርሱም ደግሞ ሊቀበልህ ይመጣል፥ ከእርሱም ጋር አራት መቶ ሰዎች አሉ።
7 ፤ ያዕቆብም እጅግ ፈርቶ ተጨነቀ፤ ከእርሱም ጋር ያሉትን ሰዎች መንጎችንም ላሞችንም ግመሎችንም በሁለት ወገን ከፈላቸው፤
8 ፤ እንዲህም አለ። ዔሳው መጥቶ አንዱን ወገን የመታ እንደ ሆነ የቀረው ወገን ያመልጣል።
9 ፤ ያዕቆብም አለ። የአባቴ የአብርሃም አምላክ ሆይ፥ የአባቴም የይስሐቅ አምላክ ሆይ። ወደ ምድርህ ወደ ተወለድህበትም ስፍራ ተመለስ፥ በጎነትንም አደርግልሃለሁ ያልኸኝ እግዚአብሔር ሆይ፤
10 ፤ ለባሪያህ ከሠራኸው ከምሕረትህና ከእውነትህም ሁሉ ትንሽ ስንኳ የማይገባኝ ነኝ፤ በትሬን ብቻ ይዤ ይህን ዮርዳኖስን ተሻግሬ ነበርና፥ አሁን ግን የሁለት ክፍል ሠራዊት ሆንሁ።
11 ፤ ከወንድሜ ከዔሳው እጅ አድነኝ፤ መጥቶ እንዳያጠፋኝ፥ እናቶችንም ከልጆች ጋር እንዳያጠፋ እኔ እፈራዋለሁና።
12 ፤ አንተም። በእርግጥ መልካም አደርግልሃለሁ፥ ዘርህንም ከብዛቱ የተነሣ እንደማይቈጠር እንደ ባሕር አሸዋ አደርጋለሁ ብለህ ነበር።
13 ፤ በዚያችም ሌሊት ከዚያው አደረ። ከያዘውም ሁሉ ለወንድሙ ለዔሳው እጅ መንሻን አወጣ፤
14 ፤ ሁለት መቶ እንስት ፍየሎችንና ሀያ የፍየል አውራዎችን፥ ሁለት መቶ እንስት በጎችንና ሀያ የበግ አውራዎችን፥
15 ፤ ሠላሳ የሚያጠቡ ግመሎችን ከግልገሎቻቸው ጋር፥ አርባ ላም፥ አሥር በሬ፥ ሀያ እንስት አህያ፥ አሥርም የእህያ ግልገሎችን።
16 ፤ መንጎቹን በየወገኑ ከፍሎ በባሪያዎቹ እጅ አደረጋቸው፤ ባሪያዎቹንም። በፊቴ እለፉ መንጋውንና መንጋውንም አራርቁት አለ።
17 ፤ የፊተኛውንም እንዲህ ብሎ አዘዘው። ወንድሜ ዔሳው ያገኘህ እንደሆነ። አንተ የማን ነህ? ወዴትስ ትሄዳለህ? በፊትህ ያለው ይህስ የማን ነው? ብሎ የጠየቀህም እንደ ሆነ፥
18 ፤ በዚያን ጊዜ አንተ። ለጌታዬ ለዔሳው እጅ መንሻ የሰደደው የባሪያህ የያዕቆብ ነው፤ እርሱም ደግሞ እነሆ ከኋላችን ነው በለው።
19 ፤ እንዲሁም ሁለተኛውንና ሦስተኛውን ከመንጎችም በኋላ የሚሄዱትን ሁሉ እንዲሁ ብሎ አዘዘ። ዔሳውን ባገኛችሁት ጊዜ ይህንኑ ነገር ንገሩት፤
20 ፤ እንዲህም በሉት። እነሆ ባሪያህ ያዕቆብ ከኋላችን ነው። በፊቴ በሚሄደው እጅ መንሻ እታረቀዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ ምናልባት ይራራልኛል ፊቱንም አያለሁ ብሎአልና።
21 ፤ እጅ መንሻው ከእርሱ ቀድሞ አለፈ፤ እርሱ ግን በዚያች ሌሊት በሰፈር አደረ።
22 ፤ በዚያች ሌሊትም ተነሣ፥ ሁለቱን ሚስቶቹንና ሁለቱን ባሪያዎቹን አሥራ አንዱንም ልጆቹን ወስዶ የያቦቅን ወንዝ ተሻገረ።
23 ፤ ወሰዳቸውም ወንዙንም አሻገራቸው፥ ከብቱንም ሁሉ አሻገረ።
24 ፤ ያዕቆብ ግን ለብቻው ቀረ፤ አንድ ሰውም እስከ ንጋት ድረስ ይታገለው ነበር።
25 ፤ እንዳላሸነፈውም ባየ ጊዜ የጭኑን ሹልዳ ነካው፤ ያዕቆብም የጭኑ ሹልዳ ሲታገለው ደነዘዘ።
26 ፤ እንዲህም አለው። ሊነጋ አቀላልቶአልና ልቀቀኝ። እርሱም። ካልባረክኸኝ አልለቅቅህም አለው።
27 ፤ እንዲህም አለው። ስምህ ማን ነው? እርሱም። ያዕቆብ ነኝ አለው።
28 ፤ አለውም። ከእንግዲህ ወዲህ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ ያዕቆብ አይባል፤ ከእግዚአብሔር ከሰውም ጋር ታግለህ አሸንፈሃልና።
29 ፤ ያዕቆብም። ስምህን ንገረኝ ብሎ ጠየቀው። እርሱም። ስሜን ለምን ትጠይቃለህ? አለው። በዚያም ስፍራ ባረከው።
30 ፤ ያዕቆብም። እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁ፥ ሰውነቴም ድና ቀረች ሲል የዚያን ቦታ ስም Dኒኤል ብሎ ጠራው።
31 ፤ Dኒኤልንም ሲያልፍ ፀሐይ ወጣችበት፥ እርሱም በጭኑ ምክንያት ያነክስ ነበር።
32 ፤ ስለዚህም የእስራኤል ልጆች እስከ ዛሬ ድረስ የወርችን ሹልዳ አይበሉም፤ የያዕቆብን ጭን ይዞ የወርችን ሹልዳ አደንዝዞአልና።q ቍ@