ኦሪት ዘፍጥረት. Chapter 34

1 ፤ ለያዕቆብ የወለደችለት የልያ ልጅ ዲናም የዚያን አገር ሴቶች ልጆችን ለማየት ወጣች።
2 ፤ የአገሩ አለቃ የኤዊያዊ ሰው የኤሞር ልጅ ሴኬም አያት፤ ወሰዳትም ከእርስዋም ጋር ተኛ፥ አስነወራትም።
3 ፤ ልቡናውም በያዕቆብ ልጅ በዲና ፍቅር ተነደፈ፥ ብላቴናይቱንም ወደዳት፥ ልብዋንም ደስ በሚያሰኛት ነገር ተናገራት።
4 ፤ ሴኬምም አባቱን ኤሞርን። ይህችን ብላቴና አጋባኝ ብሎ ነገረው።
5 ፤ ያዕቆብም ልጁን ዲናን እንዳስነወራት ሰማ፤ ልጆቹም ከከብቶቻቸው ጋር በምድረ በዳ ነበሩ፤ ያዕቆብም እስኪመጡ ድረስ ዝም አለ።
6 ፤ የሴኬም አባት ኤሞርም ይነግረው ዘንድ ወደ ያዕቆብ ወጣ።
7 ፤ የያዕቆብም ልጆች ይህንን በሰሙ ጊዜ ከምድረ በዳ መጡ፤ የያዕቆብን ልጅ በመተኛቱ በእስራኤል ላይ ስንፍናን ስላደረገ አዘኑ፥ እጅግም ተቈጡ፤ እንዲህ አይደረግምና።
8 ፤ ኤሞርም እንዲህ ብሎ ነገራቸው። ልጄ ሴኬም በልጃችሁ ፍቅር ልቡ ተነድፎአልና ሚስት እንድትሆነው እባካችሁ እርስዋን ስጡት።
9 ፤ ጋብቾችም ሁኑን፤ ሴቶች ልጆቻችሁን ስጡን፥ እናንተም የእኛን ሴቶች ልጆች ውሰዱ።
10 ፤ ከእኛም ጋር ተቀመጡ፥ ምድሪቱም በፊታችሁ ናት፤ ኑሩባት፥ ነግዱም፥ ግዙአትም።
11 ፤ ሴኬምም አባትዋንና ወንድሞችዋን እንዲህ አለ። በፊታችሁ ሞገስን ባገኝ የምትሉኝን እሰጣለሁ።
12 ፤ ብዙ ማጫና እጅ መንሻ አምጣ በሉኝ፥ በነገራችሁኝም መጠን እሰጣለሁ፤ ይህችን ብላቴና ግን አጋቡኝ።
13 ፤ የያዕቆብም ልጆች ለሴኬምና ለአባቱ ለኤሞር በተንኰል መለሱ፥ እኅታቸውን ዲናን አርክሶአታልና፤
14 ፤ እንዲህም አሉአቸው። እኅታችንን ላልተገረዘ ሰው ለመስጠት ይህንን ነገር እናደርግ ዘንድ አይቻለንም፤ ይህ ነውር ይሆንብናልና።
15 ፤ እንደ እኛ ሆናችሁ ወንዶቻችሁን ሁሉ ብትገርዙ በዚህ ብቻ እሺ እንላችኋለን፤
16 ፤ ሴቶች ልጆቻችንን እንሰጣችኋለን፥ የእናንተንም ሴቶች ልጆች እንወስዳለን፤ አንድ ሕዝብም ሆነን ከእናንተ ጋር እንኖራለን።
17 ፤ ትገረዙ ዘንድ እኛን ባትሰሙ ግን ልጃችንን ይዘን እንሄዳለን።
18 ፤ ነገራቸውም በኤሞር ልጅ በሴኬምና በኤሞር ዘንድ የተወደደ ሆነ።
19 ፤ ብላቴናውም ያሉትን ያደርግ ዘንድ አልዘገየም፥ የያዕቆብን ልጅ ወድዶአልና፤ እርሱም በአባቱ ቤት ካሉት ሁሉ የከበረ ነበረ።
20 ፤ ኤሞርና ሴኬም ልጁም ወደ ከተማቸው አደባባይ ገቡ፥ ለከተማቸውም ሰዎች እንዲህ ብለው ነገሩ።
21 ፤ እነዚህ ሰዎች በእኛ ዘንድ የሰላም ሰዎች ናቸው፤ በምድራችን ይቀመጡ፥ ይነግዱባትም፥ እነሆም ምድሪቱ ሰፊ ናት፤ ሴቶች ልጆቻቸውን እንውሰድ፥ ለእነርሱም ሴቶች ልጆቻችንን እንስጥ።
22 ፤ ነገር ግን አንድ ሕዝብ ሆነን ከእኛ ጋር ይቀመጡ ዘንድ በዚህ ነገር ብቻ እሺ ይሉናል፤ እነርሱ እንደ ተገረዙ ወንዶቻችንን ሁሉ ብንገርዝ።
23 ፤ ከብቶቻቸውም ያላቸውም ሁሉ እንስሶቻቸውም ሁሉ ለእኛ አይደሉምን? በዚህ ነገር ብቻ እሺ ያልናቸው እንደ ሆነ ከእኛ ጋር ይቀመጣሉ።
24 ፤ ከከተማይቱም አደባባይ የሚወጡ ሁሉ ኤሞርንና ልጁን ሴኬምን እሺ አሉ፤ ከከተማይቱ አደባባይ የሚወጡት ወንዶች ሁሉ ተገረዙ።
25 ፤ ሦስተኛም ቀን በሆነ ጊዜ እጅግ ቆስለው ሳሉ፥ የዲና ወንድሞች የያዕቆብ ልጆች ስምዖንና ሌዊ እየራሳቸው ሰይፋቸውን ይዘው ሳይፈሩ ወደ ከተማ ገቡ፥ ወንዱንም ሁሉ ገደሉ፤
26 ፤ ኤሞርንና ልጁን ሴኬምንም በሰይፍ ገደሉ፥ እኅታቸውን ዲናንም ከሴኬም ቤት ይዘው ወጡ።
27 ፤ የያዕቆብም ልጆች እኅታቸውን ዲናን ሰለ አረከሱአት ወደ ሞቱት ገብተው ከተማይቱን ዘረፉ፤
28 ፤ በጎቻቸውንም ላሞቻቸውንም አህዮቻቸውንም በውጭም በከተማም ያለውን ወሰዱ።
29 ፤ ሀብታቸውን ሁሉ ሕፃናቶቻቸውንና ሴቶቻቸውንም ሁሉ ማረኩ፥ በቤት ያለውንም ሁሉ ዘረፉ።
30 ፤ ያዕቆብም ሌዊንና ስሞዖንን እንዲህ አለ። በዚች አገር በሚኖሩ በከነዓናውያንና በፌርዛውያን ሰዎች የተጠላሁ ታደርጉኝ ዘንድ እኔን አስጨነቃችሁኝ፤ እኔ በቍጥር ጥቂት ነኝ፤ እነርሱ በእኔ ላይ ይሰበሰቡና ይመቱኛል፤ እኔም ከወገኔ ጋር እጠፋለሁ።
31 ፤ እነርሱም። በጋለሞታ እንደሚደረግ በእኅታችን ያደርግባትን? አሉ። a