ኦሪት ዘፍጥረት. Chapter 35
1 ፤ እግዚአብሔርም ያዕቆብን አለው። ተነሥተህ ወደ ቤቴል ውጣ፥ በዚያም ኑር፤ ከወንድምህ ከዔሳው ፊት በሸሸህ ጊዜ ለተገለጠልህ ለእግዚአብሔርም መሠውያውን አድርግ።
2 ፤ ያዕቆብም ለቤተ ሰቡና ከእርሱ ጋር ላሉት ሁሉ እንዲህ አለ። እንግዶቹን አማልክት ከመካከላችሁ አስወግዱ፥ ንጹሐንም ሁኑ፥ ልብሳችሁንም ለውጡ፤
3 ፤ ተነሥተንም ወደ ቤቴል እንውጣ፤ በዚያም በመከራዬ ጊዜ ለሰማኝ፥ በሄድሁበትም መንገድ ከእኔ ጋር ለነበረው ለእግዚአብሔር መሠውያን አደርጋለሁ።
4 ፤ በእጃቸው ያሉትንም እንግዶችን አማልክት ሁሉ በጆሮአቸውም ያሉትን ጕትቾች ለያዕቆብ ሰጡት፤ ያዕቆብም በሴኬም አጠገብ ካለችው የአድባር ዛፍ በታች ቀበራቸው።
5 ፤ ተነሥተውም ሄዱ፤ የእግዚአብሔርም ፍርሃት በዙሪያቸው ባሉት ከተሞች ሁሉ ወደቀ፥ የያዕቆብንም ልጆች ለማሳደድ አልተከተሉአቸውም።
6 ፤ ያዕቆብም፥ እርሱ ከእርሱ ጋርም የነበሩት ሰዎች ሁሉ፥ በከነዓን ምድር ወዳለችው ወደ ሎዛ መጡ፤ እርስዋም ቤቴል ናት።
7 ፤ በዚያም መሰውያውን ሠራ፥ የዚያንም ቦታ ስም ኤልቤቴል ብሎ ጠራው፤ እርሱ ከወንድሙ ፊት በሸሸበት ጊዜ እግዚአብሔር በዚያ ተገልጦለት ነበርና።
8 ፤ የርብቃ ሞግዚት ዲቦራም ሞተች፥ በቤቴልም ከአድባር ዛፍ በታች ተቀበረች፤ ስሙም አሎንባኩት ተብሎ ተጠራ።
9 ፤ እግዚአብሔርም ለያዕቆብ ከሁለት ወንዞች መካከል ከሶርያ ከተመለሰ በኋላ እንደ ገና ተገለጠለት፥ ባረከውም።
10 ፤ እግዚአብሔርም። ስምህ ያዕቆብ ነው፤ ከእንግዲህም ወዲህ ስምህ ያዕቆብ ተብሎ አይጠራ፥ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ አለ፤ ስሙንም እስራኤል ብሎ ጠራው።
11 ፤ እግዚአብሔርም አለው። ሁሉን ቻይ አምላክ እኔ ነኝ፤ ብዛ፥ ተባዛም፤ ሕዝብና የአሕዛብ ማኅበር ከአንተ ይሆናል፥ ነገሥታትም ከጕልበትህ ይወጣሉ።
12 ፤ ለአብርሃምና ለይስሐቅም የሰጠኋትን ምድር ለአንተ እሰጣለሁ፥ ከአንተም በኋላ ለዘርህ ምድሪቱን እሰጣለሁ።
13 ፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ከተነጋገረበት ስፍራ ወደ ላይ ወጣ።
14 ፤ ያዕቆብም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በተነጋገረበት ቦታ የድንጋይ ሐውልት ተከለ፤ የመጠጥ መሥዋዕትንም በእርሱ ላይ አፈሰሰ፥ ዘይትንም አፈሰሰበት።
15 ፤ ያዕቆብም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር የተነጋገረበትን ያን ቦታ ቤቴል ብሎ ጠራው።
16 ፤ ከቤቴልም ተነሡ፤ ወደ ኤፍራታም ሊደርሱ ጥቂት ሲቀራቸው ራሔልን ምጥ ያዛት፥ በምጡም ተጨነቀች።
17 ፤ ምጡም ባስጨነቃት ጊዜ አዋላጂቱ። አትፍሪ፥ ይኸኛው ደግሞ ወንድ ልጅ ይሆንሻልና አለቻት።
18 ፤ እርስዋም ስትሞት ነፍስዋ በምትወጣበት ጊዜ ስሙን ቤንኦኒ ብላ ጠራችው፤ አባቱ ግን ብንያም አለው።
19 ፤ ራሔልም ሞተች፥ ወደ ኤፍራታ በምትወስድም መንገድ ተቀበረች፤ እርስዋም ቤተልሔም ናት።
20 ፤ ያዕቆብም በመቃብርዋ ላይ ሐውልት አቆመ፤ እርሱም እስከ ዛሬ የራሔል የመቃብርዋ ሐውልት ነው።
21 ፤ እስራኤልም ከዚያ ተነሣ፥ ድንኳኑንም ከጋዴር ግንብ በስተ ወዲያ ተከለ።
22 ፤ እስራኤልም በዚያች አገር በተቀመጠ ጊዜ ሮቤል ሄደ የአባቱንም ቁባት ባላን ተገናኛት፤ እስራኤልም ሰማ። የያዕቆብም ልጆች አሥራ ሁለት ናቸው፤
23 ፤ የልያ ልጆች፤ የያዕቆብ በኵር ልጅ ሮቤል፥ ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ ይሳኮር፥ ዛብሎን፤
25 ፤ የራሔል ልጆች፤ ዮሴፍ፥ ብንያም፤ የራሔል ባርያ የባላ ልጆችም፤ ዳን፥ ንፍታሌም፤
26 ፤ የልያ ባሪያ የዘለፋ ልጆችም፤ ጋድ፥ አሴር፤ እነዚህ በሁለቱ ወንዞች መካከል በሶርያ የተወለዱለት የያዕቆብ ልጆች ናቸው።
27 ፤ ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ አብርሃምና ይስሐቅ እንግዶች ሆነው ወደ ተቀመጡባት ወደ መምሬ ወደ ቂርያትአርባቅ እርስዋም ኬብሮን ወደምትባለው መጣ።
28 ፤ የይስሐቅም ዕድሜ መቶ ሰማንያ ዓመት ሆነ።
29 ፤ ይስሐቅም ነፍሱን ሰጠ፥ ሞተም፤ ሸምግሎ ዕድሜንም ጠግቦ ወደ ወገኖቹ ተከማቸ፤ ልጆቹም ዔሳውና ያዕቆብ ቀበሩት።