ኦሪት ዘፍጥረት. Chapter 19
1 ፤ ሁለቱም መላእክት በመሸ ጊዜ ወደ ሰዶም ገቡ፤ ሎጥም በሰዶም በር ተቀምጦ ነበር። ሎጥም ባያቸው ጊዜ ሊቀበላቸው ተነሣ፤ ፊቱንም ደፍቶ ወደ ምድር ሰገደ፥ አላቸውም።
2 ፤ ጌቶቼ ሆይ፥ ወደ ባሪያችሁ ቤት አቅኑ፥ ከዚያም እደሩ፥ እግራችሁንም ታጠቡ፤ ነገ ማልዳችሁም መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ። እነርሱም። በአደባባዩ እናድራለን እንጂ፥ አይሆንም አሉት።
3 ፤ እጅግም ዘበዘባቸው፤ ወደ እርሱም አቀኑ፥ ወደ ቤቱም ገቡ፤ ማዕድ አቀረበላቸው፥ ቂጣንም ጋገረ እነርሱም በሉ።
4 ፤ ገናም ሳይተኙ የዚያች ከተማ የሰዶም ሰዎች፥ ከብላቴናው ጀምሮ እስከ ሽማግሌው ድረስ በየስፍራው ያለው ሕዝብ ሁሉ፥ ቤቱን ከበቡት።
5 ፤ ሎጥንም ጠርተው እንዲህ አሉት። በዚህ ሌሊት ወደ ቤትህ የገቡት ሰዎች ወዴት ናቸው? እናውቃቸው ዘንድ ወደ እኛ አውጣቸው።
6 ፤ ሎጥም ወደ እነርሱ ወደ ደጅ ወጣ መዝጊያውንም በኋላው ዘጋው፤
7 ፤ እንዲህም አለ። ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህን ክፉ ነገር አታድርጉ፤
8 ፤ እነሆ፥ ወንድን ያላወቁ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉኝ፤ እነርሱን ላውጣላችሁ፥ እንደ ወደዳችሁም አድርጓቸው፤ በእነዚህ ሰዎች ብቻ ምንም አታድርጉ፥ እነርሱ በጣራዬ ጥላ ሥር ገብተዋልና።
9 ፤ እነርሱም። ወዲያ ሂድ አሉት። ደግሞም እንዲህ አሉ። ይህ ሰው በእንግድነት ለመኖር መጣ፥ ፍርዱንም ይፈርድ ዘንድ ይፈልጋል፤ አሁን በአንተ ከእነርሱ ይልቅ ክፉ እናደርግብሃለን። ሎጥንም እጅግ ተጋፉት፥ የደጁንም መዝጊያ ለመስበር ቀረቡ።
10 ፤ ሁለቱም ሰዎች እጃቸውን ዘርግተው ሎጥን ወደ እነርሱ ዘንድ ወደ ቤት አገቡት መዝጊያውንም ዘጉት።
11 ፤ በቤቱ ደጃፍ የነበሩትንም ሰዎች ከታናሻቸው ጀምሮ እስከ ታለቃቸው ድረስ አሳወሩአቸው፤ ደጃፉንም ለማግኘት ሲፈልጉ ደከሙ።
12 ፤ ሁለቱም ሰዎች ሎጥን አሉት። ከዚህ ሌላ ማን አለህ? አማችም ቢሆን ወንድ ልጅም ቢሆን ወይም ሴት ልጅ ብትሆን በከተማይቱ ያለህን ሁሉ ከዚህ ስፍራ አስወጣቸው፤
13 ፤ እኛ ይህን ስፍራ እናጠፋለንና፥ ጩኸታቸው በእግዚአብሔር ፊት ትልቅ ሆኖአልና፤ እናጠፋውም ዘንድ እግዚአብሔር ሰድዶናል።
14 ፤ ሎጥም ወጣ፥ ልጆቹን ለሚያገቡት ለአማቾቹም ነገራቸው፥ አላቸውም። ተነሡ፤ ከዚህ ስፍራ ውጡ፤ እግዚአብሔር ይህችን ከተማ ያጠፋልና። ለአማቾቹ ግን የሚያፌዝባቸው መሰላቸው።
15 ፤ ጎህም በቀደደ ጊዜ መላእክት ሎጥን። ተነሣ፥ ሚስትህንና ከዚህ ያሉትን ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ውሰድ፤ በከተማይቱ ኃጢአት እንዳትጠፋ እያሉ ያስቸኵሉት ነበር።
16 ፤ እርሱም በዘገየ ጊዜ እግዚአብሔር ስላዘነለት እነዚያ ሰዎች የእርሱን እጅ የሚስቱንም እጅ የሁለቱን የሴቶች ልጆቹንም እጅ ይዘው አወጡትና በከተማይቱ ውጭ አስቀመጡት።
17 ፤ ወደ ሜዳም ካወጡአቸው በኋላ እንዲህ አለው። ራስህን አድን፤ ወደ ኋላህ አትይ፥ በዚህም ዙሪያ ሁሉ አትቁም እንዳትጠፋም ወደ ተራራው ሸሽተህ አምልጥ።
18 ፤ ሎጥም፤ አላቸው። ጌቶቼ ሆይ፥ እንዲህስ አይሁን፤
19 ፤ እነሆ ባሪያህ በፊትህ ሞገስን አግኝቶአል፥ ነፍሴን ለማዳን ያደረግህልኝን ምሕረትህንም አብዝተሃል፤ ክፉ እንዳያገኘኝና እንዳልሞት ወደ ተራራ ሸሽቼ አመልጥ ዘንድ አልችልም፤
20 ፤ እነሆ ይህች ከተማ ወደ እርስዋ ሸሽቶ ለማምለጥ ቅርብ ናት፥ እርስዋም ትንሽ ናት፤ ነፍሴን ለማዳን ወደ እርስዋ ሸሽቼ ላምልጥ፤ እርስዋ ትንሽ ከተማ አይደለችምን?
21 ፤ እርሱም አለው። የተናገርሃትን ከተማ እንዳላጠፋት እነሆ በዚህ ነገር የለመንኸኝን ተቀብዬሃለሁ፤
22 ፤ በቶሎ ወደዚያ ሸሽትህ አምልጥ፤ ወደዚያ እስክትደርስ ድረስ ምንም አደርግ ዘንድ አልችልምና። ስለዚህም የዚያች ከተማ ስም ዞዓር ተባለ።
23 ፤ ሎጥ ወደ ዞዓር በገባ ጊዜ ፀሐይ በምድር ላይ ወጣች።
24 ፤ እግዚአብሔርም በሰዶምና በገሞራ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሰማይ እሳትና ዲን አዘነበ፤
25 ፤ እነዚያንም ከተሞች፥ በዙሪያቸው ያለውንም ሁሉ፥ በከተሞቹም የሚኖሩትን ሁሉ፥ የምድሩንም ቡቃያ ሁሉ ገለበጠ።
26 ፤ የሎጥም ሚስት ወደ ኋላዋ ተመለከተች፥ የጨው ሐውልትም ሆነች።
27 ፤ አብርሃምም በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ ወደ ነበረበት ስፍራ ለመሄድ ማልዶ ተነሣ፤
28 ፤ ወደ ሰዶምና ወደ ገሞራ በዚያች አገር ወዳለውም ምድር ሁሉ ተመለከተ፤ እነሆም የአገሪቱ ጢስ እንደ እቶን ጢስ ሲነሣ አየ።
29 ፤ እግዚአብሔርም እነዚያን የአገር ከተሞች ባጠፋ ጊዜ አብርሃምን አሰበው፤ ሎጥ ተቀምጦበት የነበረውንም ከተማ ባጠፋ ጊዜ ከዚያ ጥፋት መካከል ሎጥን አወጣው።
30 ፤ ሎጥም ከዞዓር ወጣ፤ በዞዓር ይቀመጥ ዘንድ ስለ ፈራም ከሁለቱ ሴቶች ልጆቹ ጋር በተራራ ተቀመጠ፤ በዋሻም ከሁለቱ ሴቶች ልጆቹ ጋር ተቀመጠ።
31 ፤ ታላቂቱም ታናሺቱን አለቻት። አባታችን ሸመገለ፥ በምድርም ሁሉ እንዳለው ልማድ ሊገናኘን የሚችል ሰው ከምድር ላይ የለም፤
32 ፤ ነዪ አባታቻንንም የወይን ጠጅ እናጠጣውና ከእርሱ ጋር እንተኛ፥ ከአባታችንም ዘር እናስቀር።
33 ፤ በዚያችም ሌሊት አባታቸውን የወይን ጠጅ አጠጡት፤ ታላቂቱም ገባች፥ ከአባትዋም ጋር ተኛች፤ እርሱም ስትተኛና ስትነሣ አላወቀም።
34 ፤ በነጋውም ታላቂቱ ታናሺቱን አለቻት። እነሆ ትናንት ከአባቴ ጋር ተኛሁ፤ ዛሬ ሌሊት ደግሞ የወይን ጠጅ እናጠጣው አንቺም ግቢና ከእርሱ ጋር ተኚ፥ ከአባታችንም ዘር እናስቀር።
35 ፤ አባታቸውንም በዚያች ሌሊት ደግሞ የወይን ጠጅ አጠጡት፤ ታናሺቱም ገብታ ከእርሱ ጋር ተኛች፤ እርሱም ስትተኛና ስትነሣ አላወቀም።
36 ፤ የሎጥም ሁለቱ ሴቶች ልጆች ከአባታቸው ፀነሱ።
37 ፤ ታላቂቱም ወንድ ልጅ ወለደች ስሙንም ሞዓብ ብላ ጠራችው፤ እርሱም እስከ ዛሬ የሞዓባውያን አባት ነው።
38 ፤ ታናሺቱም ደግሞ ወንድ ልጅ ወለደች ስሙንም። የወገኔ ልጅ ስትል አሞን ብላ ጠራችው፤ እርሱም እስከ ዛሬ የአሞናውያን አባት ነው።