ኦሪት ዘፍጥረት. Chapter 45

1 ፤ ዮሴፍም በእርሱ ዘንድ ቆመው ባሉት ሰዎች ሁሉ ፊት ሊታገሥ አልተቻለውም። ሰዎቹንም ሁሉ ከፊቴ አስወጡልኝ ብሎ ጮኾ ተናገረ፤ ዮሴፍ ለወንድሞቹ ራሱን በገለጠ ጊዜ በእርሱ ዘንድ የቆመ ማንም አልነበረም።
2 ፤ ቃሉንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ፤ የግብፅ ሰዎችም ሰሙ፥ በፈርዖን ቤትም ተሰማ።
3 ፤ ዮሴፍም ለወንድሞቹ። እኔ ዮሴፍ ነኝ፤ አባቴ እስከ አሁን በሕይወቱ ነውን? አለ። ወንድሞቹም ይመልሱለት ዘንድ አልቻሉም፥ በፊቱ ደንግጠው ነበርና።
4 ፤ ዮሴፍም ወንድሞቹን። ወደ እኔ ቅረቡ አለ። ወደ እርሱም ቀረቡ። እንዲህም አላቸው። ወደ ግብፅ የሸጣችሁኝ እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ።
5 ፤ አሁንም ወደዚህ ስለ ሸጣችሁኝ አትዘኑ፥ አትቈርቈሩም፤ እግዚአብሔር ሕይወትን ለማዳን ከእናንተ በፊት ሰድዶኛልና።
6 ፤ ይህ ሁለቱ ዓመት በምድር ላይ ራብ የሆነበት ነውና፤ የማይታረስበትና የማይታጨድበት አምስት ዓመት ገና ቀረ።
7 ፤ እግዚአብሔርም በምድር ላይ ቅሬታን አስቀርላችሁ ዘንድ በታላቅ መድኃኒትም አድናችሁ ዘንድ ከእናንተ በፊት ላከኝ።
8 ፤ አሁንም እናንተ ወደዚህ የላካችሁኝ አይደላችሁም፥ እግዚአብሔር ላከኝ እንጂ፤ ለፈርዖንም እንደ አባት አደረገኝ፥ በቤቱም ሁሉ ላይ ጌታ፥ በግብፅ ምድርም ሁሉ ላይ አለቃ አደረገኝ።
9 ፤ አሁንም ፈጥናችሁ ወደ አባቴ ውጡ፥ እንዲህም በሉት። ልጅህ ዮሴፍ የሚለው ነገር ይህ ነው። እግዚአብሔር በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ጌታ አደረገኝ፤ ወደ እኔ ና፥ አትዘግይ፤
10 ፤ በጌሤምም ምድር ትቀመጣለህ፥ ወደ እኔም ትቀርባለህ፥ አንተና ልጆችህ የልጆችህም ልጆች፥ በጎችህና ላሞችህ ከብትህም ሁሉ።
11 ፤ በዚያም አንተና የቤትህ ሰዎች የአንተ የሆነው ሁሉ እንዳትቸገሩ እመግብሃለሁ የራቡ ዘመን ገና አምስት ዓመት ቀርቶአልና።
12 ፤ እነሆም ለእናንተ የተናገረቻችሁ የእኔ አፍ እንደ ሆነች የእናንተ ዓይኖች አይተዋል፥ የወንድሜ የብንያምም ዓይኖች አይተዋል።
13 ፤ ለአባቴም በግብፅ ምድር ያለኝን ክብሬን ሁሉ ያያችሁትንም ሁሉ ንገሩት፤ አባቴንም ወደዚህ ፈጥናችሁ አምጡት።
14 ፤ የወንድሙን የብንያምንም አንገት አቅፎ አለቀሰ፤ ብንያምም በአንገቱ ላይ አለቀሰ።
15 ፤ ወንድሞቹን ሁሉ ሳማቸው፥ በእነርሱም ላይ አለቀሰ፤ ከዚያም በኋላ ወንድሞቹ ከእርሱ ጋር ተጫወቱ።
16 ፤ በፈርዖንም ቤት። የዮሴፍ ወንድሞች መጡ ተብሎ ወሬ ተሰማ፤ በዚያውም ፈርዖንና ሎላልቱ ደስ ተሰኙበት።
17 ፤ ፈርዖንም ዮሴፍን አለው። ለወንድሞችህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ይህን አድርጉ፤ ከብቶቻችሁን ጭናችሁ ወደ ከነዓን ምድር ሂዱ፤
18 ፤ አባታችሁንና ቤተሰቦቻችሁን ይዛችሁም ወደ እኔ ኑ፤ እኔም የግብፅን ምድር በረከት ሁሉ እሰጣችኋለሁ፥ የምድሪቱንም ስብ ትበላላችሁ።
19 ፤ አንተም ወንድሞችህን። እንዲህ አድርጉ በላቸው፤ ከግብፅ ምድር ለሕፃናቶቻችሁ ለሴቶቻችሁም ሰረገሎችን ውሰዱ፥ አባታችሁንም ይዛችሁ ኑ፤
20 ፤ ለዕቃችሁም ሁሉ አታስቡ፥ የግብፅ በረከት ሁሉ ለእናንተ ነውና።
21 ፤ የእስራኤል ልጆችም እንደዚሁ አደረጉ፤ ዮሴፍም በፈርዖን ትእዛዝ ሰረገሎችንና ለመንገድ ስንቅ ሰጣቸው፤
22 ፤ ለሁሉም ሁለት ሁለት መለወጫ ልብስ ሰጣቸው፥ ለብንያም ግን ሦስት መቶ ብርና አምስት መለወጫ ልብስ ሰጠው።
23 ፤ ለአባቱም እንደዚሁ ሰደደ፥ የግብፅን በረከት የተሸከሙ አሥር አህዮችን፥ ደግሞም በመንገድ ለአባቱ ስንቅ ስንዴና እንጀራ የተሸከሙ አሥር ሴቶች አህዮችን።
24 ፤ ዮሴፍም ወንድሞቹን አሰናበታቸው፥ እንዲህም አላቸው። በመንገድ እርስ በርሳችሁ አትጣሉ።
25 ፤ እነርሱም ሄዱ፥ ከግብፅ አገርም ወጡ፥ ወደ ከነዓንም ምድር ከአባታቸው ከያዕቆብ ዘንድ ደረሱ።
26 ፤ እንዲህም ብለው ነገሩት። ዮሴፍ ገና በሕይወቱ ነው፥ እርሱም በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ገዥ ሆኖአል። ያዕቆብም ልቡ ደነገጠ፥ አላመናቸውም ነበርና።
27 ፤ እነርሱም ዮሴፍ የነገራቸውን ነገር ሁሉ ነገሩት፤ እርሱን ያነሡት ዘንድ ዮሴፍ የሰደዳቸውን ሰረገሎች ባየ ጊዜ የአባታቸው የያዕቆብ የነፍሱ ሕይወት ታደሰች።
28 ፤ እስራኤልም። ልጄ ዮሴፍ ገና በሕይወት ከሆነ ይበቃኛል፤ ሳልሞት እንዳየው እሄዳለሁ አለ።