መጽሐፈ ዕዝራ።. Chapter 7

1 ፤ ከዚህም ነገር በኋላ በፋርስ ንጉሥ በአርጤክስስ መንግሥት ዕዝራ የሠራያ ልጅ፥
2 ፤ የዓዛርያስ ልጅ፥ የኬልቅያስ ልጅ፥ የሰሎም ልጅ፥ የሳዶቅ ልጅ፥ የአኪጦብ ልጅ፥
3 ፤ የአማርያ ልጅ፥ የዓዛርያስ ልጅ፥ የመራዮት ልጅ፥
4 ፤ የዘራእያ ልጅ፥ የኦዚ ልጅ፥ የቡቂ ልጅ፥
5 ፤ የአቢሱ ልጅ፥ የፊንሐስ ልጅ፥ የአልዓዛር ልጅ፥ የታላቁ ካህን የአሮን ልጅ፥ ይህ ዕዝራ ከባቢሎን ወጣ፤
6 ፤ የእስራኤልም አምላክ እግዚአብሔር በሰጠው በሙሴ ሕግ ፈጣን ጸሐፊ ነበረ፤ የአምላኩም የእግዚአብሔር እጅ በእርሱ ላይ ነበረችና ንጉሡ የሻውን ሁሉ ሰጠው።
7 ፤ ከእስራኤልም ልጆች ከካህናቱም ከሌዋውያኑም ከመዘምራኑም ከበረኞቹም ከናታኒምም በንጉሡ በአርጤክስስ በሰባተኛው ዓመት አያሌዎች ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ።
8 ፤ በንጉሡም በሰባተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ወደ ኢየሩሳሌም ደረሰ።
9 ፤ በመጀመሪያውም ወር በአንደኛው ቀን ከባቢሎን ሊወጣ ጀመረ፥ መልካሚቱም የአምላኩ እጅ በእርሱ ላይ ነበረችና በአምስተኛ ወር በመጀመሪያው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም ደረሰ።
10 ፤ ዕዝራም የእግዚአብሔርን ሕግ ይፈልግና ያደርግ ዘንድ፥ ለእስራኤልም ሥርዓትንና ፍርድን ያስተምር ዘንድ ልቡን አዘጋጅቶ ነበር።
11 ፤ ንጉሡም አርጤክስስ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ቃልና ለእስራኤል የሆነውን ሥርዓት ይጽፍ ለነበረው ለጸሐፊው ለካህኑ ለዕዝራ የሰጠው የደብዳቤው ግልባጭ ይህ ነው።
12 ፤ ከንጉሠ ነገሥት ከአርጤክስስ ለሰማይ አምላክ ሕግ ጸሐፊ ለካህኑ ለዕዝራ፥ ሙሉ ሰላም ይሁን፤
13 ፤ በመንግሥቴ ውስጥ ካሉ ከእስራኤል ሕዝብ ከካህናቱና ከሌዋውያኑም ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ የሚወድድ ሁሉ ከአንተ ጋር እንዲሄድ አዝዣለሁ።
14 ፤ በእጅህ እንዳለችው እንደ አምላክህ ሕግ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ትጐበኝ ዘንድ፥
15 ፤ ንጉሡንና አማካሪዎቹም መኖሪያው በኢየሩሳሌም ለሆነው ለእስራኤል አምላክ በፈቃዳቸው ያቀረቡትን ብርና ወርቅ፥
16 ፤ በባቢሎንም አውራጃ ሁሉ የምታገኘውን ብርና ወርቅ ሁሉ፥ ሕዝቡና ካህናቱም በኢየሩሳሌም ላለው ለአምላካቸው ቤት በፈቃዳቸው የሚያቀርቡትን ትወስድ ዘንድ በንጉሡና በሰባቱ አማካሪዎች ተልከሃልና፤
17 ፤ ስለዚህ በዚህ ገንዘብ ወደፈኖችንና አውራ በጎችን ጠቦቶችንም የእህላቸውንና የመጠጣቸውን ቍርባን ተግተህ ግዛ፤ በኢየሩሳሌምም ባለው በአምላካችሁ ቤት መሠዊያ ላይ አቅርባቸው።
18 ፤ ከቀረውም ብርና ወርቅ አንተና ወንድሞችህ ለማድረግ ደስ የሚያሰኛችሁን ነገር እንደ አምላካችሁ ፈቃድ አድርጉ።
19 ፤ ስለ አምላክህም ቤት አገልግሎት የተሰጠህን ዕቃ በኢየሩሳሌም አምላክ ፊት አሳልፈህ ስጥ።
20 ፤ ከዚህም በላይ ለማውጣት የሚያስፈልግህን ለአምላክህ ቤት የሚያሻውን ነገር ከንጉሡ ቤተ መዛግብት አውጣ።
21 ፤ እኔም ንጉሡ አርጤክስስ በወንዝ ማዶ ላሉት በጅሮንዶች ሁሉ ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ። የሰማይ አምላክ ሕግ ጸሐፊ ካህኑ ዕዝራ ከእናንተ የሚፈልገውን ሁሉ አዘጋጁለት፤
22 ፤ እስከ መቶ መክሊት ብርም ቢሆን፥ እስከ መቶ የቆሬስ መስፈሪያ ስንዴ፥ እስከ መቶም የባዶስ መስፈሪያ የወይን ጠጅ፥ እስከ መቶም የባዶስ መስፈሪያ ዘይት ቢሆን፥ ጨውም ያለ ልክ ቢሆን ስጡ።
23 ፤ በንጉሡና በልጆቹ መንግሥት ላይ ቍጣ እንዳይሆን፥ የሰማይ አምላክ ያዘዘው ሁሉ ለሰማይ አምላክ ቤት በሙሉ ይደረግ።
24 ፤ ደግሞም በካህናቱና በሌዋውያን በመዘምራኑም በበረኞቹም በናታኒምም በዚህም በእግዚአብሔር ቤት በሚሠሩ አገልጋዮች ላይ ግብርና ቀረጥ መጥንም እንዳይጣል ብለን እናስታውቃችኋለን።
25 ፤ አንተም ዕዝራ፥ በእጅህ እንዳለው እንደ አምላክህ ጥበብ መጠን በወንዝ ማዶ ባሉ ሕዝብ ሁሉ የአምላክህን ሕግ በሚያውቁ ሁሉ ላይ ይፈርዱ ዘንድ ዳኞችንና ፈራጆች አስነሣ፤ የማያውቁትንም አስተምሩአቸው።
26 ፤ የአምላክህንም ሕግ፥ የንጉሡንም ሕግ በማያደርግ ሁሉ ላይ ሞት ወይም ስደት ወይም ገንዘብን መወረስ ወይም ግዞት በፍጥነት ይፈረድበት።
28 ፤ በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት ያሳምር ዘንድ እንደዚህ ያለውን ነገር በንጉሡ ልብ ያኖረ፥ በንጉሡም በአማካሪዎቹም በንጉሡም ኃያላን አለቆች ሁሉ ፊት ምሕረቱን ወደ እኔ የላከ የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ። እኔም በላዬ ባለችው በአምላኬ በእግዚአብሔር እጅ በረታሁ፤ ከእኔም ጋር እንዲወጡ ከእስራኤል ዘንድ አለቆችን ሰበሰብሁ።