መጽሐፈ ዕዝራ።. Chapter 9
1 ፤ ይህም ከተፈጸመ በኋላ አለቆቹ ወደ እኔ ቀርበው። የእስራኤል ሕዝብ ካህናቱም ሌዋውያኑም እንደ ከነዓናውያን እንደ ኬጢያውያን እንደ ፌርዛውያን እንደ ኢያቡሳውያን እንደ አሞናውያን እንደ ሞዓባውያን እንደ ግብጻውያንና እንደ አሞራውያን ርኵሰት ያደርጋሉ እንጂ ከምድር አሕዛብ አልተለዩም፤
2 ፤ ለራሳቸውና ለልጆቻቸውም ሴቶች ልጆቻቸውን ወስደዋል፥ የተቀደሰውንም ዘር ከምድር አሕዛብ ጋር ደባልቀዋል፤ አስቀድሞም አለቆቹና ሹማምቶቹ በዚህ መተላለፍ መጀመሪያ ሆነዋል አሉኝ።
3 ፤ ይህንም ነገር በሰማሁ ጊዜ ልብሴንና መጐናጸፊያዬን ቀደድሁ፥ የራሴንና የጢሜንም ጠጉር ነጨሁ፥ ደንግጬም ተቀመጥሁ።
4 ፤ ስለ ምርኮኞቹም መተላለፍ የእስራኤልን አምላክ ቃል የሚፈሩ ሁሉ ወደ እኔ ተሰበሰቡ፤ እኔም እስከ ሠርክ መሥዋዕት ድረስ ደንግጬ ተቀመጥሁ።
5 ፤ በሠርክም መሥዋዕት ጊዜ ልብሴና መጐናጸፊያዬ እንደ ተቀደደ ሆኖ ከመዋረዴ ተነሣሁ፤ በጕልበቴም ተንበርክኬ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር እጄን ዘረጋሁ።
6 ፤ እንዲህም አልሁ። አምላኬ ሆይ፥ ኃጢአታችን በራሳችን ላይ በዝቶአልና፥ በደላችንም ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ ብሎአልና አምላኬ ሆይ፥ ፊቴን ወደ አንተ አነሣ ዘንድ አፍራለሁ፥ እፈራማለሁ።
7 ፤ ከአባቶቻችን ዘመን ጀምረን እስከ ዛሬ ድረስ እጅግ በድለናል፤ ዛሬም እንደ ሆነው ስለ ኃጢአታችን እኛና ንጉሦቻችን ካህናቶቻችንም ለሰይፍና ለምርኮ ለብዝበዛና ለእፍረት በምድር ነገሥታት እጅ ተጣልን።
8 ፤ አሁንም ቅሬታ ይተውልን ዘንድ፥ በተቀደሰውም ስፍራው ችንካርን ይሰጠን ዘንድ፥ አምላካችንም ዓይናችንን ያበራ ዘንድ፥ በባርነትም ሳለን ጥቂት የሕይወት መታደስን ይሰጠን ዘንድ ለጥቂት ጊዜ ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ሞገስ ተሰጥቶናል።
9 ፤ ባሪያዎች ነንና፥ አምላካችን ግን በባርነታችን አልተወንም፤ የሕይወት መታደስን ይሰጠን ዘንድ፥ የአምላካችንንም ቤት እንሠራ ዘንድ፥ የተፈታውንም እንጠግን ዘንድ፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም ቅጥር ይደረግልን ዘንድ በፋርስ ነገሥታት ፊት ምሕረቱን ሰጠን።
12 ፤ አሁንስ አምላካችን ሆይ። ትወርሱአት ዘንድ የምትገቡባት ምድር በምድር አሕዛብ ርኵሰት ረክሳለች፥ ከዳር እስከ ዳርም ድረስ ከርኵሰታቸው ከጸያፍ ሥራቸውም ተሞልታለች፤ አሁንም ትበረቱ ዘንድ፥ የምድሩንም ፍሬ ትበሉ ዘንድ፥ ለዘላለም ለልጆቻችሁ ታወርሱአት ዘንድ ሴቶች ልጆቻችሁን ለልጆቻቸው አትስጡ፥ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለልጆቻችሁ አትውሰዱ፥ ሰላማቸውንና ደኅንነታቸውንም ለዘላለም አትሹ ብለህ በባሪያዎችህ በነቢያት ያዘዝኸውን ትእዛዝ ትተናልና ከዚህ በኋላ ምን እንላለን?
13 ፤ ስለ ክፉ ሥራችንና ስለ ታላቁ በደላችን ካገኘን ነገር ሁሉ በኋላ፥ አንተ አምላካችን እንደ ኃጢአታችን ብዛት አልቀሠፍኸንም ነገር ግን ቅሬታን ሰጠኸን።
14 ፤ በውኑ ተመልሰን ትእዛዝህን እናፈርስ ዘንድ፥ ርኩስ ሥራን ከሚሠሩ ከእነዚህም አሕዛብ ጋር እንገባ ዘንድ ይገባናልን? አንተስ ቅሬታ የሌለንና የማናመልጥ እስክንሆን ድረስ እንድታጠፋን አትቈጣንም?
15 ፤ አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ዛሬም እንደ ሆነው እኛ አምልጠን ቀርተናል፤ እነሆ በፊትህ በበደላችን አለን፤ ስለዚህ በፊትህ ሊቆም የሚችል የለም።