ትንቢተ ሕዝቅኤል. Chapter 22
1 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ ትፈርዳለህን? ደም በምታፈስስ ከተማ ላይ ትፈርዳለህን? ርኵሰትዋን ሁሉ አስታውቃት።
3 ፤ እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጊዜሽ እንዲደርስ በመካከልሽ ደምን የምታፈስሺ እንድትረክሺም በራስሽ ላይ ጣዖታትን የምታደርጊ ከተማ ሆይ!
4 ፤ ባፈሰስሽው ደም በድለሻል ባደረግሽውም ጣዖታት ረክሰሻል፤ ቀንሽን አቀረብሽ ዘመንሽንም አሳጠርሽ፤ ስለዚህ ለአሕዛብ መሰደቢያ ለአገሮችም ሁሉ መሳለቂያ አደረግሁሽ።
5 ፤ አንቺ ስምሽ የረከሰ ሽብርም የሞላብሽ ሆይ፥ ወደ አንቺ የቀረቡና ከአንቺ የራቁ ይሳለቁብሻል።
6 ፤ እነሆ፥ የእስራኤል አለቆች እያንዳንዱ እንደ ችሎቱ ደም ያፈስሱ ዘንድ በአንቺ ውስጥ ነበሩ።
7 ፤ በአንቺ ውስጥ አባትንና እናትን አቃለሉ፤ በመካከልሽ በመጻተኛው ላይ በደልን አደረጉ፤ በአንቺ ውስጥ ድሀ አደጉንና መበለቲቱን አስጨነቁ።
8 ፤ ቅድሳቴንም ናቅሽ ሰንበታቴንም አረከስሽ።
9 ፤ ደምን ያፈስሱ ዘንድ ቀማኞች ሰዎች በአንቺ ውስጥ ነበሩ፤ በአንቺ ውስጥ በተራሮች ላይ በሉ፤ በመካከልሽ ሴሰኝነትን አደረጉ።
10 ፤ በአንቺ ውስጥ የአባቶቻቸውን ኀፍረተ ሥጋ ገለጡ፤ በአንቺም ውስጥ አደፍ ያለባትን አዋረዱ።
11 ፤ ሰውም በባልንጀራው ሚስት ርኵሰትን አደረገ፥ አባትም የልጁን ሚስት አረከሰ፥ በአንቺም ዘንድ ወንድም የአባቱን ልጅ እኅቱን አሳፈረ።
12 ፤ በአንቺ ውስጥ ደምን ያፈስሱ ዘንድ ጉቦን ተቀበሉ፤ አንቺም አራጣና ትርፍ ወስደሻል፥ ከባልንጀሮችሽም በቅሚያ የስስትን ትርፍ አገኘሽ፥ እኔንም ረሳሽኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
13 ፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ አንቺ ባደረግሽው ስስት በመካከልሽም በነበረው ደም ላይ እጄን አጨበጨብሁ።
14 ፤ በውኑ እኔ በማደርግብሽ ወራት ልብሽ ይታገሣልን? ወይስ እጅሽ ትጸናለችን? እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ አደርገውማለሁ።
15 ፤ ወደ አሕዛብም እበትንሻለሁ ወደ አገሮችም እዘራሻለሁ፥ ርኵሰትሽንም ከአንቺ ዘንድ አጠፋለሁ።
16 ፤ በአሕዛብም ፊት አንቺ ትረክሻለሽ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂአለሽ።
17 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
18 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤል ቤት ለእኔ እንደ አተላ ሆኑብኝ፤ እነርሱ ሁሉ በከውር ውስጥ መዳብና ቈርቈሮ ብረትና እርሳስ ናቸው፤ የብር አተላ ናቸው።
19 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሁላችሁ አተላ ሆናችኋልና ስለዚህ፥ እነሆ፥ በኢየሩሳሌም ውስጥ እሰበስባችኋለሁ።
20 ፤ እንዲያቀልጡት እሳት ያናፉበት ዘንድ ብርንና መዳብን ብረትንና እርሳስን ቈርቈሮንም በከውር እንደሚሰበስቡ፥ እንዲሁ በቍጣዬና በመዓቴ እሰበስባችኋለሁ፥ በዚያም ውስጥ እጨምራችኋለሁ አቀልጣችሁማለሁ።
21 ፤ አሰበስባችሁማለሁ የመዓቴንም እሳት አናፋባችኋለሁ በውስጡም ትቀልጣላችሁ።
22 ፤ ብርም በከውር ውስጥ እንደሚቀልጥ፥ እንዲሁ በውስጡዋ ትቀልጣላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር መዓቴን እንዳፈሰስሁባችሁ ታውቃላችሁ።
23 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
24 ፤ የሰው ልጅ ሆይ። አንቺ ያልነጻሽ በቍጣም ቀን ያልዘነበብሽ ምድር ነሽ በላት።
25 ፤ በውስጥዋ ያሉ ነቢያት እንደሚጮኽና እንደሚናጠቅ አንበሳ አንድ ሆነው ተማማሉ፤ ነፍሶችን በልተዋል፥ ብልጥግናና ሀብትን ወስደዋል፥ በውስጥዋም መበለቶችን አብዝተዋል።
26 ፤ ካህናቶችዋም ሕጌን በድለዋል ቅድሳቴንም አርክሰዋል፤ ቅዱስ በሆነና ቅዱስ ባልሆነ መካከልም አልለዩም፥ በንጹሕና በርኩስ መካከል ያለውን ልዩነት አላስታወቁም፤ ዓይናቸውንም ከሰንበታቴ ሰወሩ እኔም በመካከላቸው ረከስሁ።
27 ፤ በውስጥዋ ያሉ አለቆችዋ የስስትን ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ደምን ያፈስሱ ዘንድ ነፍሶችንም ያጠፉ ዘንድ እንደሚናጠቁ ተኵላዎች ናቸው።
28 ፤ እግዚአብሔርም ሳይናገር ነቢያቶችዋ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል እያሉ ከንቱን ራእይ በማየት የሐሰትንም ምዋርት ለእነርሱ በማምዋረት ያለ ገለባ በጭቃ ይመርጓቸዋል።
29 ፤ የምድርን ሕዝብ ግፍ አደረጉ ቅሚያም ሠሩ፤ ድሆችንና ችግረኞችን አስጨነቁ፥ መጻተኛውንም በደሉ።
30 ፤ ቅጥርን የሚጠግንን፥ ምድሪቱንም እንዳላጠፋት በፈረሰበት በኩል በፊቴ የሚቆምላትን ሰው በመካከላቸው ፈለግሁ፥ ነገር ግን አላገኘሁም።
31 ፤ ስለዚህ ቍጣዬን አፈሰስሁባቸው፥ በመዓቴም እሳት አጠፋኋቸው፤ መንገዳቸውንም በራሳቸው ላይ መለስሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።