ትንቢተ ሕዝቅኤል. Chapter 39
1 ፤ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ በጎግ ላይ ትንቢትን ተናገር እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የሞሳሕና የቶቤል ዋነኛ አለቃ ጎግ ሆይ፥ እነሆ፥ እኔ በአንተ ላይ ነኝ፤
2 ፤ እመልስሃለሁ፥ እነዳህማለሁ፥ ከሰሜንም ዳርቻ እጐትትሃለሁ፥ ወደ እስራኤልም ተራሮች አመጣሃለሁ።
3 ፤ ከግራ እጅህም ቀስትህን አስጥልሃለሁ፥ ከቀኝ እጅህም ፍላጾችህን አስረግፍሃለሁ።
4 ፤ አንተና ጭፍሮችህ ሁሉ ከአንተም ጋር ያሉ ሕዝብ በእስራኤል ተራሮች ላይ ትወድቃላችሁ፤ ለሚናጠቁ ወፎች ሁሉና ለምድር አራዊትም መብል አድርጌ እሰጥሃለሁ።
5 ፤ አንተ በምድር ፊት ላይ ትወድቃለህ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
6 ፤ በማጎግም ላይ ሳይፈሩም በደሴቶች በሚቀመጡ ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
7 ፤ ቅዱሱም ስሜ በሕዝቤ በእስራኤል መካከል ይታወቅ ዘንድ አደርጋለሁ፥ ቅዱሱንም ስሜን ከእንግዲህ ወዲህ አላስረክስም፤ አሕዛብም እግዚአብሔር፥ የእስራኤል ቅዱስ፥ እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
8 ፤ እነሆ፥ ይመጣል ይሆንማል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ያልሁት ቀን ይህ ነው።
9 ፤ በእስራኤልም ከተሞች የሚኖሩ ይወጣሉ፥ የጦር መሣሪያዎችንም በእሳት ያቃጥላሉ፤ አላባሽ ጋሻንና ጋሻን፥ ቀስትንና ፍላጻዎችን፥ ጎመድንና ጦርንም ያቃጥላሉ፤ ሰባት ዓመት በእሳት ያቃጥሉአቸዋል።
10 ፤ በጦር መሣሪያው እሳትን ያነድዳሉ እንጂ እንጨትን ከምድረ በዳ አይወስዱም ከዱርም አይቈርጡም፤ የገፈፉአቸውንም ይገፍፋሉ የበዘበዙአቸውንም ይበዘብዛሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
11 ፤ በዚያም ቀን በእስራኤል ዘንድ በባሕር ምሥራቅ የሚያልፉበትን ሸለቆ የመቃብርን ስፍራ ለጎግ እሰጣለሁ፥ የሚያልፉትንም ይከለክላል፤ በዚያም ጎግንና ብዛቱን ሁሉ ይቀብራሉ፤ የሸለቆውንም ስም ሐሞንጎግ ብለው ይጠሩታል።
12 ፤ ምድሩንም ያጸዱ ዘንድ የእስራኤል ቤት ሰዎች ሰባት ወር ይቀብሩአቸዋል፥
13 ፤ የምድርም ሕዝብ ሁሉ ይቀብሩአቸዋል፥ በተመሰገንሁበትም ቀን ለክብር ይሆንላችኋል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
14 ፤ ምድርንም ለማጽዳት በምድሩ ላይ ወድቀው የቀሩትን የሚቀብሩ፥ ዘወትር በምድሩ ላይ የሚዞሩትን ሰዎች ይቀጥራሉ፤ ከሰባት ወርም በኋላ ይመረምራሉ።
15 ፤ በምድርም የሚዞሩት ያልፋሉ፤ የሰውንም አጥንት ቢያዩ፥ ቀባሪዎች በሐሞን ጎግ ሸለቆ እስኪቀብሩት ድረስ ምልክት ያኖሩበታል።
16 ፤ ደግሞም የከተማይቱ ስም ሐሞና ይባላል። እንዲሁ ምድሪቱን ያጸዳሉ።
17 ፤ አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ለወፎች ሁሉና ለምድር አራዊት ሁሉ እንዲህ በላቸው። ኑ፥ ተከማቹ፥ ሥጋንም ትበሉ ዘንድ ደምንም ትጠጡ ዘንድ በእስራኤል ተራሮች ላይ ወደማርድላችሁ መሥዋዕት፥ እርሱም ታላቅ መሥዋዕት፥ ከየስፍራው ሁሉ ተሰብሰቡ።
18 ፤ የኃያላኑን ሥጋ ትበላላችሁ የምድርንም አለቆች፥ የአውራ በጎችንና የጠቦቶችን፥ የፍየሎችንና የወይፈኖችን፥ የባሳንን ፍሪዳዎች ሁሉ፥ ደም ትጠጣላችሁ።
19 ፤ እኔም ከማርድላችሁ መሥዋዕት እስክትጠግቡ ድረስ ጮማ ትበላላችሁ እስክትሰክሩም ድረስ ደም ትጠጣላችሁ።
20 ፤ በሰደቃዬም ከፈረሶችና ከፈረሰኞች፥ ከኃያላንና ከሰልፈኞች ሁሉ ትጠግባላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
21 ፤ ክብሬንም በአሕዛብ መካከል አኖራለሁ አሕዛብም ሁሉ ያደርግሁትን ፍርዴን፥ በላያቸውም ያኖርኋትን እጄን ያያሉ።
22 ፤ ከእንግዲህም ወዲያ የእስራኤል ቤት እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
23 ፤ አሕዛብም የእስራኤል ቤት በኃጢአታቸው ምክንያት እንደ ተማረኩ ያውቃሉ፤ ስለ በደሉኝ እኔም ፊቴን ከእነርሱ ስለ ሸሸግሁ፥ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፌ ሰጠኋቸው፥ እነርሱም ሁሉ በሰይፍ ወደቁ።
24 ፤ እንደ ርኵሰታቸውም እንደ መተላለፋቸውም መጠን አደረግሁባቸው ፊቴንም ከእነርሱ ሸሸግሁ።
25 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። አሁን የያዕቆብን ምርኮ እመልሳለሁ ለእስራኤልም ቤት ሁሉ እራራለሁ፥ ስለ ቅዱስ ስሜም እቀናለሁ።
27 ፤ ማንም ሳያስፈራቸው በምድራቸው ተዘልለው በተቀመጡ ጊዜ ከአሕዛብም ዘንድ በመለስኋቸው ጊዜ ከጠላቶቻቸውም ምድር በሰበሰብኋቸው ጊዜ በብዙ አሕዛብም ፊት በተቀደስሁባቸው ጊዜ፥ እፍረታቸውንና የበደሉኝን በደላቸውን ሁሉ ይሸከማሉ።
28 ፤ እኔም ወደ አሕዛብ አስማርኬአቸዋለሁና፥ ወደ ገዛ ምድራቸውም ሰብስቤአቸዋለሁና እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ በዚያም ከእነርሱ አንድ ሰው ከእንግዲህ ወዲያ አልተውም፥
29 ፤ ፊቴንም ከእነርሱ ከእንግዲህ ወዲህ አልሸሽግም፤ መንፈሴን በእስራኤል ቤት ላይ አፍስሻለሁና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።