ትንቢተ ሕዝቅኤል. Chapter 6
1 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።
2 ፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ እስራኤል ተራሮች አቅና ትንቢትም ተናገርባቸው።
3 ፤ እንዲህም በል። የእስራኤል ተራሮች ሆይ፥ የጌታን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር ለተራሮችና ለኮረብቶች ለምንጮችና ለሸለቆች እንዲህ ይላል። እኔ፥ እነሆ፥ እኔ ሰይፍን አመጣባችኋለሁ የኮረብታው መስገጃዎቻችሁንም አጠፋለሁ።
4 ፤ መሠዊያዎቻችሁም ይፈርሳሉ፥ የፀሐይም ምስሎቻችሁ ይሰበራሉ፤ ተወግተውም የሞቱትን ሰዎቻችሁን በጣዖቶቻችሁ ፊት እጥላለሁ።
5 ፤ የእስራኤልንም ልጆች ሬሳዎች በጣዖቶቻቸው ፊት አኖራለሁ፥ አጥንቶቻችሁንም በመሠዊያዎቻችሁ ዙሪያ እበትናለሁ።
6 ፤ በምትኖሩበትም ስፍራ ሁሉ ከተሞቹ ይፈርሳሉ፥ የኮረብታው መስገጃዎችም ሁሉ ውድማ ይሆናሉ፥ መሠዊያዎቻችሁም ይፈርሳሉ ባድማም ይሆናሉ፥ ጣዖቶቻችሁም ይሰበራሉ ያልቃሉም፥ የፀሐይም ምስሎቻችሁ ይቈረጣሉ፥ ሥራችሁም ይሻራል።
7 ፤ ተወግተውም የሞቱት በመካከላችሁ ይወድቃሉ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
8 ፤ ነገር ግን በአገሮች በተበተናችሁ ጊዜ ከሰይፍ ያመለጡትን ቅሬታ በአሕዛብ መካከል አስቀርላችኋለሁ።
9 ፤ ከእናንተም የዳኑት ከእኔ በራቀው በአመንዝራ ልባቸውና ጣዖቶቻቸውን በተከተሉ በአመንዝራ ዓይኖቻቸው የተሰበርሁትን እኔን ወደ እነርሱ በተማረኩት አሕዛብ መካከል ሆነው ያስቡኛል፤ በርኵሰታቸውም ሁሉ ስላደረጉት ክፋት ራሳቸውን ይጸየፋሉ።
10 ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ ይህን ክፉ ነገር አደርግባቸው ዘንድ መናገሬ በከንቱ አይደለም።
11 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእጅህ አጨብጭብ በእግርህም አሸብሽብ እንዲህም በል። በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ይወድቃሉና ስለ እስራኤል ቤት ስለ አስጸያፊ ሥራዎቻቸው ሁሉ ወዮ!
12 ፤ በሩቅ ያለው በቸነፈር ይሞታል፥ በቅርብም ያለው በሰይፍ ይወድቃል፥ የቀረውና የዳነውም በራብ ይሞታል፤ እንዲሁ መዓቴን እፈጽምባቸዋለሁ።
13 ፤ ተወግተውም የሞቱ ሰዎቻቸው በጣዖቶቻቸው መካከልና በመሠዊያዎቻቸው ዙሪያ፥ ለጣዖቶቻቸው ጣፋጭ ሽታ ባቀረቡበት ስፍራ፥ ከፍ ባለው ኮረብታ ሁሉ በተራሮችም ራስ ሁሉ ላይ፥ ከለመለመውም ዛፍ ሁሉ በታች ቅጠሉም ከበዛ ከአድባር ዛፍ ሁሉ በታች በሆኑ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
14 ፤ እጄንም እዘረጋባቸዋለሁ፥ በሚኖሩበትም ስፍራ ሁሉ ምድሪቱን ከዴብላታ ምድረ በዳ ይልቅ ውድማና በረሃ አደርጋታለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።