ኦሪት ዘጸአት. Chapter 2

1 ፤ ከሌዊ ወገንም አንድ ሰው ሄዶ የሌዊን ልጅ አገባ።
2 ፤ ሴቲቱም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅም ወለደች፤ መልካምም እንደሆነ ባየች ጊዜ ሦስት ወር ሸሸገችው።
3 ፤ ደግሞም ልትሸሽገው ባልቻለች ጊዜ፥ የደንገል ሣጥን ለእርሱ ወስዳ ዝፍትና ቅጥራን ለቀለቀችው፤ ሕፃኑንም አኖረችበት፥ በወንዝም ዳር ባለ በቄጠማ ውስጥ አስቀመጠችው።
4 ፤ እኅቱም የሚደረግበትን ታውቅ ዘንድ በሩቅ ቆማ ትጎበኘው ነበር።
5 ፤ የፈርዖንም ልጅ ልትታጠብ ወደ ወንዝ ወረደች፤ ደንገጥሮችዋም በወንዝ ዳር ይሄዱ ነበር፤ ሣጥኑንም በቄጠማ ውስጥ አየች፥ ደንገጥርዋንም ልካ አስመጣችው።
6 ፤ በከፈተችውም ጊዜ ሕፃኑን አየች፥ እነሆም ሕፃኑ ያለቅስ ነበር፤ አዘነችለትም። ይህ ከዕብራውያን ልጆች አንድ ነው አለች።
7 ፤ እኅቱም ለፈርዖን ልጅ። ሕፃኑን ታጠባልሽ ዘንድ ሄጄ የምታጠባ ሴት ከዕብራውያን ሴቶች ልጥራልሽን? አለቻት።
8 ፤ የፈርዖንም ልጅ። ሂጂ አለቻት፤ ብላቴናይቱም ሄዳ የሕፃኑን እናት ጠራች።
9 ፤ የፈርዖንም ልጅ። ይህን ሕፃን ወስደሽ አጥቢልኝ፥ ዋጋሽንም እሰጥሻለሁ አለቻት። ሴቲቱም ሕፃኑን ወስዳ አጠባችው።
10 ፤ ሕፃኑም አደገ፥ ወደ ፈርዖንም ልጅ ዘንድ አመጣችው፥ ለእርስዋም ልጅ ሆነላት። እኔ ከውኃ አውጥቼዋለሁና ስትልም ስሙን ሙሴ ብላ ጠራችው።
11 ፤ በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ፤ ሙሴ ጎበዝ በሆነ ጊዜ ወደ ወንድሞቹ ወጣ፥ የሥራቸውንም መከራ ተመለከተ፤ የግብፅም ሰው የወንድሞቹን የዕብራውያንን ሰው ሲመታ አየ።
12 ፤ ወዲህና ወዲያም ተመለከተ፥ ማንንም አላየም፥ ግብፃዊውንም ገደለ፥ በአሸዋም ውስጥ ሸሸገው።
13 ፤ በሁለተኛውም ቀን ወጣ፥ ሁለቱም የዕብራውያን ሰዎች ሲጣሉ አየ፤ በዳዩንም። ለምን ባልንጀራህን ትመታዋለህ? አለው።
14 ፤ ያም። በእኛ ላይ አንተን አለቃ ወይስ ዳኛ ማን አደረገህ? ወይስ ግብፃዊውን እንደ ገደልኸው ልትገድለኝ ትሻለህን? አለው። ሙሴም። በእውነት ይህ ነገር ታውቆአል ብሎ ፈራ።
15 ፤ ፈርዖንም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ሙሴን ሊገድለው ፈለገ። ሙሴ ግን ከፈርዖን ፊት ኰበለለ፥ በምድያምም ምድር ተቀመጠ፤ በውኃም ጕድጓድ አጠገብ ዐረፈ።
16 ፤ ለምድያምም ካህን ሰባት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም መጥተው ውኃ ቀዱ፥ የአባታቸውንም በጎች ሊያጠጡ የውኃውን ገንዳ ሞሉ።
17 ፤ እረኞችም መጥተው ገፉአቸው፤ ሙሴ ግን ተነሥቶ ረዳቸው፥ በጎቻቸውንም አጠጣላቸው።
18 ፤ ወደ አባታቸው ወደ ራጉኤልም በመጡ ጊዜ። ስለ ምን ዛሬ ፈጥናችሁ መጣችሁ? አላቸው።
19 ፤ እነርሱም። አንድ የግብፅ ሰው ከእረኞች እጅ አዳነን፥ ደግሞም ቀዳልን፥ በጎቻችንንም አጠጣ አሉ።
20 ፤ ልጆቹንም። እርሱ ወዴት ነው? ለምንስ ያንን ሰው ተዋችሁት? ጥሩት እንጀራም ይብላ አላቸው።
21 ፤ ሙሴም ከዚያ ሰው ጋር ሊቀመጥ ወደደ፤ ልጁንም ሲፓራን ለሙሴ ሚስት ትሆነው ዘንድ ሰጠው።
22 ፤ ወንድ ልጅም ወለደች። በሌላ ምድር መጻተኛ ነኝ ሲል ስሙን ጌርሳም ብሎ ጠራው።
23 ፤ ከዚያም ከብዙ ቀን በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የግብፅ ንጉሥ ሞተ፤ የእስራኤልም ልጆች ከባርነት የተነሣ አለቀሱ፥ ጮኹም፥ ስለ ባርነታቸውም ጩኸታቸው ወደ እግዚአብሔር ወጣ።
24 ፤ እግዚአብሔርም የለቅሶአቸውን ድምፅ ሰማ፥ እግዚአብሔርም ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን አሰበ።
25 ፤ እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆች አየ፥ እግዚአብሔርም በእነርሱ ያለውን ነገር አወቀ።