መጽሐፈ መክብብ. Chapter 4
1 ፤ እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አየሁ፤ እነሆም፥ የተገፉት ሰዎች እንባ ነበረ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፤ በሚገፉአቸውም እጅ ኃይል ነበረ፥ እነርሱን ግን የሚያጽናናቸው አልነበረም።
2 ፤ እኔም እስከ ዛሬ በሕይወት ካሉት ይልቅ በቀድሞ ዘመን የሞቱትን አመሰገንሁ፤
3 ፤ ከእነዚህም ከሁለቱ ይልቅ ገና ያልተወለደው ከፀሐይም በታች የሚደረገውን ግፍ ያላየው ይሻላል።
4 ፤ ደግሞም የሰውን ድካምና የብልሃት ሥራውን ሁሉ ተመለከትሁ፥ በባልንጀራውም ዘንድ ቅንዓት እንዲያስነሣ አየሁ፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።
5 ፤ ሰነፍ እጆቹን ኮርትሞ ይቀመጣል፤ የገዛ ሥጋውንም ይበላል።
6 ፤ በድካምና ነፋስን በመከተል ከሁለት እጅ ሙሉ ይልቅ አንድ እጅ ሙሉ በዕረፍት ይሻላል።
7 ፤ እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ከንቱን ነገር አየሁ።
8 ፤ አንድ ሰው ብቻውን አለ፥ ሁለተኛም የለውም ልጅም ሆነ ወንድም የለውም፤ ለድካሙ ግን መጨረሻ የለውም፥ ዓይኖቹም ከባለጠግነት አይጠግቡም። ለማን እደክማለሁ፥ ሰውነቴንስ መልካሙን ነገር ለምን እነፍጋታለሁ? ይላል። ይህም ደግሞ ከንቱ ነገር ክፉም ጥረት ነው።
9 ፤ ድካማቸው መልካም ዋጋ አለውና አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል።
10 ፤ ቢወድቁ አንዱ ሁለተኛውን ያነሣዋልና፤ አንዱ ብቻውን ሆኖ በወደቀ ጊዜ ግን የሚያነሣው ሁለተኛ የለውምና ወዮለት።
11 ፤ ሁለቱም በአንድነት ቢተኙ ይሞቃቸዋል፤ አንድ ብቻውን ግን እንዴት ይሞቀዋል?
12 ፤ አንዱም አንዱን ቢያሸንፍ ሁለቱ በፊቱ ይቆማሉ፤ በሦስትም የተገመደ ገመድ ፈጥኖ አይበጠስም።
13 ፤ ድሀና ጠቢብ ብላቴና ተግሣጽን መቀበል ከእንግዲህ ወዲህ ከማያውቅ ከሰነፍ ሽማግሌ ንጉሥ ይሻላል።
14 ፤ ምንም በመንግሥቱ አገር ደግሞ ችግረኛ ሆኖ ቢወለድ፥ ከግዞቱ ቤት ወደ መንግሥት ወጥቶአልና።
15 ፤ ከፀሐይ በታች የሚሄዱትን ሕያዋን ሁሉ በእርሱ ፋንታ ከሚነሣው ከሌላው ጎበዝ ጋር ሆነው አየሁ።
16 ፤ ከእርሱ በፊት የተገዙለት ሕዝብ ሁሉ አይቈጠሩም፤ በኋላ የሚመጡት ግን በእርሱ ደስ አይላቸውም። ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።