ኦሪት ዘዳግም. Chapter 13
1 ፤ በመካከልህም ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ቢነሣ፥ ምልክትም ተአምራትም ቢሰጥህ፥
2 ፤ እንደ ነገረህም ምልክቱ ተአምራቱም ቢፈጸም፥ እርሱም። ሄደን የማታውቃቸውን ሌሎች አማልክት እንከተል እናምልካቸውም ቢልህ፥
3 ፤ አምላካችሁን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁ በፍጹምም ነፍሳችሁ ትወድዱት እንደ ሆነ ያውቅ ዘንድ አምላካችሁ እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ ነውና የዚያን ነቢይ ቃል ወይም ያን ሕልም አላሚ አትስማ።
4 ፤ አምላካችሁን አግዚአብሔርን ተከተሉ፥ እርሱንም ፍሩ፥ ትእዛዙንም ጠብቁ፥ ቃሉንም ስሙ፥ እርሱንም አምልኩ፥ ከእርሱም ጋር ተጣበቁ።
5 ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ትሄድባት ዘንድ ካዘዘህ መንገድ ሊያወጣህ፥ ከግብፅ ምድር ካወጣችሁ ከባርነትም ቤት ካዳናችሁ ከአምላካችሁ ከእግዚአብሔር ሊያስታችሁ ተናግሮአልና ያ ነቢይ ወይም ያ ሕልም አላሚ ይገደል፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከመካከልህ አርቅ።
6 ፤7፤ የእናትህ ልጅ ወንድምህ ወይም ወንድ ልጅህ ወይም ሴት ልጅህ ወይም በብብትህ ያለች ሚስትህ ወይም እንደ ነፍስህ ያለ ወዳጅህ በስውር። ና፥ ሄደን ከምድር ዳር ጀምሮ እስከ ምድር ዳር ድረስ ወደ አንተ የቀረቡት ከአንተም የራቁት አንተን ከብበውህ ያሉ አሕዛብ ከሚያመልኩአቸው አማልክት፥ አንተም አባቶችህም የማታውቋቸውን ሌሎች አማልክት እናምልክ ብሎ ቢያስትህ፥ እሺ አትበለው፥
8 ፤ አትስማውም፤ ዓይንህም አይራራለት፥ እትማረውም፥ አትሸሽገውም፤
9 ፤ ነገር ግን ፈጽመህ ግደለው፤ እርሱን ለመግደል በፊት የአንተ እጅ፥ ከዚያም በኋላ የሕዝቡ ሁሉ እጅ በላዩ ትሁን።
10 ፤ ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ካወጣህ ከአምላክህ ከእግዚአብሔር ሊያርቅህ ወድዶአልና እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ውገረው።
11 ፤ እስራኤልም ሁሉ ሰምተው ይፈራሉ፥ እንዲህም ያለ ክፉ ሥራ እንደ ገና በአንተ መካከል አያደርጉም።
13 ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ልትኖርባት በሚሰጥህ በአንዲቱ ከተማህ። ክፋተኞች ሰዎች ከእናንተ ዘንድ ወጥተው። ሄደን የማታውቋቸውን ሌሎችን አማልክት እናምልክ ብለው የከተማቸውን ሰዎች አሳቱ ሲሉ ወሬ ብትሰማ፥
14 ፤ ትፈልጋለህ፥ ትመረምራለህም፥ ትጠይቃለህም፤ እነሆም፥ እውነት ቢሆን፥ ይህም ክፉ ነገር በመካከልህ እንደ ተደረገ እርግጥ ሆኖ ቢገኝ፥
15 ፤ የዚያችን ከተማ ሰዎች በሰይፍ ስለት ፈጽሞ ትመታቸዋለህ፤ ከተማይቱን፥ በእርስዋም ያለውን ሁሉ፥ እንስሳውንም በሰይፍ ስለት ታጠፋቸዋለህ።
16 ፤ ዕቃዋንም ሁሉ ወደ አደባባይዋ ትሰበሰባለህ፥ ከተማይቱንም ዕቃዋንም ሁሉ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በእሳት ፈጽመህ ታቃጥላለህ፤ ለዘላለምም ወና ትሆናለች፥ ደግሞም አትሠራም።
18 ፤ ዛሬም እኔ የማዝዝህን ትእዛዝ ሁሉ ትጠብቅ ዘንድ፥ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ደስ የሚያሰኘውን ታደርግ ዘንድ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ስትሰማ፥ የእግዚአብሔር መቅሠፍት ቍጣ ይመለስ ዘንድ፥ ለአባቶችህም እንደ ማለላቸው ይምርህ ዘንድ፥ ይራራልህም ዘንድ፥ ያበዛህም ዘንድ፥ እርም ከሆነው አንዳች ነገር በእጅህ አይንጠልጠልብህ።