ኦሪት ዘዳግም. Chapter 16

1 ፤ በአቢብ ወር አምላክህ እግዚአብሔር በሌሊት ከግብፅ ስላወጣህ የአቢብን ወር ጠብቅ፥ የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ፋሲካ አድርግበት።
2 ፤ አምላክህ እግዚአብሔር በዚያ ስሙ ይጠራበት ዘንድ በመረጠው ስፍራ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ከበግና ከላም መንጋ ፋሲካ ሠዋ።
3 ፤ የቦካውን እንጀራ ከእርሱ ጋር አትብላ፤ ከግብፅ አገር በችኰላ ስለ ወጣህ ከግብፅ አገር የወጣህበትን ቀን በዕድሜህ ሁሉ ታስብ ዘንድ የመከራን እንጀራ፥ ቂጣ እንጀራ፥ ሰባት ቀን ከእርሱ ጋር ብላ።
4 ፤ ሰባት ቀንም በአገርህ ሁሉ እርሾ አይታይም፤ በመጀመሪያው ቀን ማታ ከሠዋኸው ሥጋ እስከ ነገ ድረስ ምንም አይደር።
5 ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ከሰጠህ ከአገርህ ደጆች በማንኛይቱም ፋሲካን ትሠዋ ዘንድ አይገባህም።
6 ፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ስሙ ይጠራበት ዘንድ በመረጠው በዚያ ስፍራ ከግብፅ በወጣህበት ወራት፥ ፀሐይ ሲገባ፥ ማታ ፋሲካን ሠዋ።
7 ፤ አምላክህ እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ ታበስለዋለህ፥ ትበላውማለህ፤ በነጋውም ተነሥተህ ወደ ድንኳንህ ትሄዳለህ።
8 ፤ ስድስት ቀን ቂጣ እንጀራ ብላ፤ በሰባተኛውም ቀን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ጉባኤ ይሁን፤ ሥራን ሁሉ አታድርግበት።
9 ፤ ሰባት ሳምንትም ትቈጥራለህ፤ መከሩን ማጨድ ከምትጀምርበት ቀን ጀምሮ ሰባት ሳምንት መቍጠር ትጀምራለህ።
10 ፤ አምላክህ እግዚአብሔር በባረከህ መጠን በፈቃድህ የምታቀርበውን አምጥተህ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የሰባቱ ሱባዔ በዓል ታደርጋለህ።
11 ፤ አንተ፥ ወንድ ልጅህና ሴት ልጅህ፥ ወንድ ባሪያህና ሴት ባሪያህ፥ በአገርህም ደጅ ውስጥ ያለው ሌዋዊ፥ በመካከልህም ያሉት መጻተኛና ድሀ አደግ መበለትም አምላክህ እግዚአብሔር በዚያ ስሙ ይጠራበት ዘንድ በሚመርጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበላችሁ።
12 ፤ አንተም በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህ አስብ፤ ይህንንም ሥርዓት ጠብቅ፥ አድርገውም።
13 ፤ ከአውድማህና ከመጥመቂያህ ፍሬህን በሰበሰብህ ጊዜ የዳስ በዓል ሰባትን ቀን ትጠብቃለህ።
14 ፤ አንተም፥ ወንድ ልጅህና ሴት ልጅህ፥ ወንድ ባሪያህና ሴት ባሪያህ፥ በአገርህም ደጅ ውስጥ ያለ ሌዋዊና መጻተኛ፥ ድሀ አደግና መበለትም በበዓል ደስ ይበላችሁ።
15 ፤ አምላክህ እግዚአብሔር በፍሬህ ሁሉ በእጅህም ሥራ ሁሉ ይባርክሃልና እግዚአብሔር በመረጠው ስፍራ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ሰባት ቀን በዓል ታደርጋለህ፤ አንተም ፈጽሞ ደስ ይልሃል።
16 ፤ በዓመት ሦስት ጊዜ፥ በቂጣ በዓል፥ በሰባቱ ሱባዔም በዓል፥ በዳስም በዓል ወንዶችህ ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት እርሱ በመረጠው ስፍራ ይታዩ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ባዶ እጃቸውን አይታዩ።
17 ፤ አምላክህ እግዚአብሔር በረከት እንደ ሰጠህ መጠን እያንዳንዱ ሰው እንደ ችሎታው ይስጥ።
18 ፤ አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ በአገርህ ደጅ ሁሉ በየነገዶችህ ፈራጆችንና አለቆችን ሹም፤ ለሕዝቡም ቅን ፍርድ ይፍረዱ።
19 ፤ ፍርድን አታጣምም፤ ፊት አይተህም አታድላ፤ ጉቦ የጥበበኞችን ዓይን ያሳውራልና፥ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና ጉቦ አትቀበል።
20 ፤ በሕይወት ትኖር ዘንድ፥ አምላክህ እግዚአብሔርም የሚሰጥህን ምድር ትወርስ ዘንድ እውነተኛውን ፍርድ ተከተል።
21 ፤ ለአንተ በምትሠራው በአምላክህ በእግዚአብሔር መሠዊያ አጠገብ ከማናቸውም ዛፍ የማምለኪያ ዐፀድ አድርገህ አትትከል።
22 ፤ አምላክህ እግዚአብሔርም የሚጠላውን ሐውልት ለአንተ አታቁም።