ኦሪት ዘዳግም. Chapter 8

1 ፤ በሕይወት እንድትኖሩ፥ እንድትበዙም፥ እግዚአብሔርም ለአባቶቻችሁ ወደ ማለላቸው ምድር ገብታችሁ እንድትወርሱአት፥ ዛሬ ለአንተ የማዝዘውን ትእዛዝ ሁሉ ታደርጉ ዘንድ ጠብቁ።
2 ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ይፈትንህ ዘንድ፥ በልብህም ያለውን ትእዛዙን ትጠብቅ ወይም አትጠብቅ እንደሆነ ያውቅ ዘንድ፥ ሊያስጨንቅህ በእነዚህ በአርባ ዓመታት በምድረ በዳ የመራህን መንገድ ሁሉ አስብ።
3 ፤ ሰውም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ነገር ሁሉ በሕይወት እንዲኖር እንጂ ሰው በእንጀራ ብቻ በሕይወት እንዳይኖር ያስታውቅህ ዘንድ አስጨነቀህ፥ አስራበህም፥ አንተም ያላወቅኸውን አባቶችህም ያላወቁትን መና አበላህ።
4 ፤ በእነዚህ አርባ ዓመታት የለበስኸው ልብስ አላረጀም፥ እግርህም አላበጠም።
5 ፤ ሰውም ልጁን እንደሚገሥፅ እንዲሁም አምላክህ እግዚአብሔር አንተን እንዲገሥጽ በልብህ አስተውል።
6 ፤ በመንገዱም እንድትሄድ እርሱንም እንድትፈራ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቅ።
7 ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ወደ መልካም ምድር፥ ከሸለቆና ከኮረብታ የሚመነጩ የውኃ ጅረቶችና ፈሳሾች ምንጮችም ወዳሉባት ምድር፥
8 ፤ ስንዴ ገብስም ወይንም በለስም ሮማንም ወይራም ማርም ወደ ሞሉባት ምድር፥
9 ፤ ሳይጎድልህ እንጀራን ወደምትበላባት አንዳችም ወደማታጣባት ምድር፥ ድንጋይዋ ብረት ወደ ሆነ፥ ከተራራዋም መዳብ ወደሚማስባት ምድር ያገባሃል።
10 ፤ ትበላማለህ፥ ትጠግብማለህ፥ ስለሰጠህም ስለመልካሚቱ ምድር አምላክህን እግዚአብሔርን ትባርካለህ።
11 ፤ ዛሬ እኔ አንተን የማዝዘውን ትእዛዙንና ፍርዱን ሥርዓቱንም ባለመጠበቅ አምላክህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ፤
12 ፤ ከበላህና ከጠገብህ በኋላ፥ መልካምም ቤት ሠርተህ ከተቀመጥህበት በኋላ፥
13 ፤ የላምና የበግ መንጋ ከበዛልህ በኋላ፥ ብርህና ወርቅህም ያለህም ሁሉ ከበዛልህ በኋላ፥ ልብህ እንዳይጓደድ፤
14 ፤ ከግብፅም ምድር ከባርነት ቤት ያወጣህን፥
15 ፤ እባብና ጊንጥ ጥማትም ባለባት፥ ውኃም በሌለባት፥ በታላቂቱና በምታስፈራው ምድረ በዳ የመራህን፥ ከጭንጫ ድንጋይም ውኃን ያወጣልህን፥
16 ፤ በመጨረሻም ዘመን መልካም ያደርግልህ ዘንድ ሊፈትንህ ሊያዋርድህም አባቶችህ ያላወቁትን መና በምድረ በዳ ያበላህን አምላክህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ፤
17 ፤ በልብህም። ጉልበቴ የእጄም ብርታት ይህን ሀብት አመጣልኝ እንዳትል።
18 ፤ ነገር ግን ዛሬ እንደ ሆነ ለአባቶችህ የማለውን ቃል ኪዳን ያጸና ዘንድ፥ ሀብት ለማከማቸት እርሱ ጉልበት ሰጥቶሃልና አምላክህን እግዚአብሔርን አስብ።
19 ፤ አምላክህንም እግዚአብሔርን ብትረሳ፥ ሌሎችንም አማልክት ብትከተል ብታመልካቸውም ብትሰግድላቸውም፥ ፈጽሞ እንድትጠፉ እኔ ዛሬውኑ እመሰክርባችኋለሁ።
20 ፤ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ስላልሰማችሁ እግዚአብሔር ከፊታችሁ እንደሚያጠፋቸው እንደ አሕዛብ እንዲሁ እናንተ ትጠፋላችሁ።