ኦሪት ዘዳግም

1 ፤ በዮርዳኖስ ማዶ በምድረ በዳ፥ በዓረባ ውስጥ በኤርትራ ባሕር ፊት ለፊት፥ በፋራን በጦፌልም በላባንም በሐጼሮትም በዲዛሃብም መካከል ሳሉ፥ ሙሴ ለእስራኤል ሁሉ የነገራቸው ቃል ይህ ነው።
2 ፤ በሴይር ተራራ መንገድ ከኮሬብ እስከ ቃዴስ በርኔ ድረስ የአሥራ አንድ ቀን መንገድ ነው።
3 ፤4፤ በአርባኛው ዓመት በአሥራ አንደኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን፥ ሙሴ፥ በሐሴቦን ተቀምጦ የነበረውን የአሞራውያንን ንጉሥ ሴዎንን፥ በአስታሮትና በኤድራይ ተቀምጦ የነበረውን የባሳንን ንጉሥ ዐግን ከመታ በኋላ፥ እግዚአብሔር ስለ እነርሱ ያዘዘውን ሁሉ ለእስራኤል ልጆች ነገራቸው።
5 ፤ በዮርዳኖስ ማዶ በሞዓብ ምድር ሙሴ እንዲህ ብሎ ይህችን ሕግ ይገልጥ ጀመር።
6 ፤ አምላካችን እግዚአብሔር በኮሬብ እንዲህ ብሎ ተናገረን። በዚህ ተራራ የተቀመጣችሁት በቃ፤
7 ፤ ተመልሳችሁ ተጓዙ፤ ወደ ተራራማው ወደ አሞራውያን አገር ወደ ድንበሮቹም ሁሉ፥ በዓረባም በደጋውም በቈላውም በደቡብም በባሕርም ዳር ወዳሉ ወደ ከነዓናውያን ምድር፥ ወደ ሊባኖስም እስከ ታላቁ ወንዝም እስከ ኤፍራጥስ ድረስ ሂዱ።
8 ፤ እነሆ፥ ምድሪቱን በፊታችሁ አድርጌአለሁ፤ ግቡ፥ እግዚአብሔር ለእነርሱ ከእነርሱም በኋላ ለዘራቸው ይሰጣት ዘንድ ለአባቶቻችሁ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማለላቸውንም ምድር ውረሱ።
9 ፤ በዚያም ዘመን እንዲህ ብዬ ተናገርኋችሁ። እኔ ብቻዬን ልሸከማችሁ አልችልም፤
10 ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር አብዝቶአችኋል፥ እነሆም፥ እናንተ ዛሬ እንደ ሰማይ ከዋክብት ብዛት ናችሁ።
11 ፤ የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር በዚህ ቁጥር ላይ እልፍ አእላፋት ይጨምር፥ እንደ ተናገራችሁም ይባርካችሁ።
12 ፤ እኔ ብቻዬን ድካምችሁን ሸክማችሁንም ክርክራችሁንም እሸከም ዘንድ እንዴት እችላለሁ?
13 ፤ ከእናንተ ከየነገዳችሁ ጥበበኞች አስተዋዮዎችም አዋቂዎችም የሆኑትን ሰዎች ምረጡ፥ እኔም በላያችሁ አለቆች አደርጋቸዋለሁ።
14 ፤ እናንተም። እናደርገው ዘንድ የተናገርኸው ይህ ነገር መልካም ነው ብላችሁ መለሳችሁልኝ።
15 ፤ ጥበበኞችና አዋቂዎች የሆኑትን የነገዶቻችሁን አለቆች መረጥሁ፥ በእናንተም ላይ አለቆች የሻለቆችም የመቶ አለቆችም የአምሳ አለቆችም የአሥር አለቆችም ገዦችም በየነገዶቻቸው አደረግኋቸው።
16 ፤ በዚያን ጊዜም። የወንድሞቻችሁን ነገር ስሙ፤ በሰውና በወንድሙ ከእርሱም ጋር ባለው መጻተኛ መካከል በጽድቅ ፍረዱ።
17 ፤ በፍርድም አድልዎ አታድርጉ፤ ታላቁን እንደምትሰሙ፥ ታናሹንም እንዲሁ ስሙ፤ ፍርድ ለእግዚአብሔር ነውና ከሰው ፊት አትፍሩ፤ ከነገርም አንድ ነገር ቢከብዳችሁ እርሱን ወደ እኔ አምጡት፥ እኔም እሰማዋለሁ ብዬ ፈራጆቻችሁን አዘዝኋቸው።
18 ፤ በዚያን ጊዜም ልታደርጉት የሚገባችሁን ነገር ሁሉ አዘዝኋችሁ።
19 ፤ ከኮሬብም ተጓዝን፥ አምላካችን እግዚአብሔር እንዳዘዘን በታላቁ እጅግም በሚያስፈራ በዚያ ባያችሁት ምድረ በዳ ሁሉ በኩል በተራራማው በአሞራውያን መንገድ ሄድን፤ ወደ ቃዴስ በርኔም መጣን።
20 ፤ እኔም። አምላካችን እግዚአብሔር ወደሚሰጠን ወደ ተራራማው ወደ አሞራውያን አገር መጣችሁ፤
21 ፤ እነሆ፥ አምላክህ እግዚአብሔር ምድሪቱን በፊትህ አድርጎአል፤ የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር እንዳለህ፥ ውጣ፥ ውረሳት፤ አትፍራ፥ አትደንግጥም አልኋችሁ።
22 ፤ እናንተም ሁላችሁ ወደ እኔ ቀርባችሁ። ምድሪቱን እንዲጎበኙልንና እንወጣበት ዘንድ የሚገባንን የመንገዱንና የምንገባባቸውን የእነዚያን ከተሞች ወሬ ተመልሰው እንዲነግሩን በፊታችን ሰዎች እንስደድ አላችሁኝ።
23 ፤ ያም ነገር ደስ አሰኘኝ፤ ከእናንተም አሥራ ሁለት ሰው መረጥሁ፤ ከየነገዱ ሁሉ አንድ አንድ ሰው ነበረ።
24 ፤ ሄዱም፥ ወደ ተራራማውም ወጡ፥ ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ መጥተው ጎበኙአት።
25 ፤ ከምድሪቱም ፍሬ በእጃቸው ወሰዱ፥ ወደ እኛም ይዘውት መጡ። አምላካችን እግዚአብሔር የሚሰጠን ምድር መልካም ናት ብለውም አወሩልን።
26 ፤ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ ዓመፃችሁ እንጂ ወደ እርስዋ መውጣትን እንቢ አላችሁ፤
27 ፤ በድንኳናችሁም ውስጥ እንዲህ እያላችሁ አጕረመረማችሁ። እግዚአብሔር ስለ ጠላን እንዲያጠፋን በአሞራውያን አጅ አሳልፎ ይሰጠን ዘንድ ከግብፅ ምድር አወጣን።
28 ፤ ወዴት እንወጣለን? ሕዝቡ ብዙ ነው፥ ቁመቱም ከእኛ ይረዝማል፥ ከተሞቹም ታላላቆች የተመሸጉም እስከ ሰማይም የደረሱ ናቸው፥ የዔናቅንም ልጆች ደግሞ በዚያ አየናቸው ብለው ወንድሞቻችን ልባችንን አስፈሩት።
29 ፤ እኔም አልኋችሁ። አትደንግጡ፥ ከእነርሱም አትፍሩ፤
30 ፤ በፊታችሁ የሚሄደው አምላካችሁ እግዚአብሔር፥ እናንተ ስታዩ በግብፅና በምድረ በዳ እንዳደረገላችሁ ሁሉ፥ ስለ እናንተ ይዋጋል፤
31 ፤ ወደዚህም ስፋራ እስክትመጡ ድረስ በሄዳችሁበት መንገድ ሁሉ፥ ሰው ልጁን እንዲሸከም አምላክህ እግዚአብሔር እንደተሸከመህ አንተ አይተሃል።
33 ፤ ዳሩ ግን ለሰፈራችሁ የሚገባውን ስፍራ እንዲፈልግላችሁ፥ ትሄዱበት ዘንድ የሚገባውንም መንገድ እንዲያሳያችሁ ሌሊት በእሳት፥ ቀን በደመና በፊታችሁ በመንገድ ሲሄድ የነበረውን አምላካችሁን እግዚአብሔርን በዚህ ነገር አላመናችሁም።
34 ፤ እግዚአብሔርም የቃላችሁን ድምፅ ሰምቶ ተቆጣ።
35 ፤ ለአባቶቻችሁ እሰጣት ዘንድ የማልሁላቸውን መልካሚቱን ምድር ከእነዚህ ሰዎች ከዚህ ክፉ ትውልድ ማንም አያይም፥
36 ፤ ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብ በቀር እርሱ ግን ያያታል፤ እግዚአብሔርን ፈጽሞ ተከትሎአልና የረገጣትን ምድር ለእርሱ ለልጆቹም እሰጣለሁ ብሎ ማለ።
37 ፤ እግዚአብሔርም ደግሞ በእናንተ ምክንያት በእኔ ተቆጣ እንዲህም አለ። አንተ ደግሞ ወደዚያ አትገባም፤
38 ፤ በፊትህ የሚቆም የነዌ ልጅ ኢያሱ እርሱ ወደዚያ ይገባል፤ እርሱ ለእስራኤል ምድሪቱን ያወርሳልና አደፋፍረው።
39 ፤ ደግሞ። ለምርኮ ይሆናሉ ያላችኋቸው ሕፃናቶቻችሁ፥ ዛሬም መልካሙን ከክፉ መለየት የማይችሉ ልጆቻችሁ፥ እነርሱ ወደዚያ ይገባሉ፥ ምድሪቱንም ለእነርሱ እስጣለሁ ይወርሱአታልም።
40 ፤ እናንተ ግን ተመልሳችሁ በኤርትራ ባሕር መንገድ ወደ ምድረ በዳ ሂዱ።
41 ፤ እናንተም። እግዚአብሔርን በድለናል፤ አምላካችን እግዚአብሔር እንዳዘዘን ሁሉ እንወጣለን፥ እንዋጋማለን ብላችሁ መለሳችሁልኝ። ከእናንተም ሰው ሁሉ የጦር መሣሪያውን ያዘ፥ ወደ ተራራማውም አገር መውጣትን አቀለላችሁት።
42 ፤ እግዚአብሔርም። እኔ በእናንተ መካከል አይደለሁምና በጠላቶቻችሁ ፊት እንዳትወድቁ አትውጡ፥ አትዋጉም በላቸው አለኝ። እኔም ተናገርኋችሁ፤
43 ፤ እናንተ ግን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ ዓመፃችሁ እንጂ አልሰማችሁም፤ በትዕቢታችሁም ወደ ተራራማው አገር ወጣችሁ።
44 ፤ በዚያም በተራራማው አገር ይኖሩ የነበር አሞራውያን ወጥተው ተጋጠሙአችሁ፥ ንብ እንደምታሳድድም አሳደዱአችሁ፥ እስከ ሔርማም ድረስ በሴይር መቱአችሁ።
45 ፤ ተመልሳችሁም በእግዚአብሔር ፊት አለቀሳችሁ፤ እግዚአብሔር ግን ድምፃችሁን አልሰማም፥ ወደ እናንተም አላዳመጠም።
46 ፤ እንደ ተቀመጣችሁበትም ዘመን መጠን በቃዴስ ብዙ ቀን ተቀመጣችሁ።