ትንቢተ አሞጽ. Chapter 3

1 ፤ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር በእናንተ፥ ከግብጽ ምድር ባወጣሁት ወገን ሁሉ ላይ የተናገረውን ይህን ቃል ስሙ፤
2 ፤ እንዲህም ብሎአል። እኔ ከምድር ወገን ሁሉ እናንተን ብቻችሁን አውቄአችኋለሁ፤ ስለዚህ ስለ ኃጢአታችሁ ሁሉ እበቀላችኋለሁ።
3 ፤ በውኑ ሁለት ሰዎች ሳይስማሙ በአንድነት ይሄዳሉን?
4 ፤ ወይስ አንበሳ የሚነጥቀው ነገር ሳያገኝ በጫካ ውስጥ ያገሣልን? ወይስ የአንበሳ ደቦል አንዳች ሳይዝ በመደቡ ሆኖ ይጮኻልን?
5 ፤ ወይስ ወፍ፥ አጥማጅ ከሌለው፥ በምድር ላይ በወጥመድ ይያዛልን? ወይስ ወስፈንጠር አንዳች ሳይዝ ከምድር ይፈነጠራልን?
6 ፤ ወይስ በከተማ ውስጥ መለከት ሲነፋ ሕዝቡ አይፈራምን? ወይስ ክፉ ነገር በከተማ ላይ የመጣ እንደ ሆነ ያደረገው እግዚአብሔር አይደለምን?
7 ፤ በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ለባሪያዎቹ ለነቢያት ካልነገረ በቀር ምንም አያደርግም።
8 ፤ አንበሳው አገሣ፤ የማይፈራ ማን ነው? ጌታ እግዚአብሔር ተናገረ፤ ትንቢት የማይናገር ማን ነው?
9 ፤ በአዛጦን አዳራሾችና በግብጽ ምድር አዳራሾች አውሩና። በሰማርያ ተራሮች ላይ ተሰብሰቡ፥ በውስጥዋም የሆነውን ታላቁን ውካታ፥ በመካከልዋም ያለውን ግፍ ተመልከቱ በሉ።
10 ፤ ግፍንና ቅሚያን በአዳራሾቻቸው የሚያከማቹት ቅን ነገርን ያደርጉ ዘንድ አያውቁም፥ ይላል እግዚአብሔር።
11 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በምድሪቱ ዙሪያ ጠላት ይመጣል፤ ብርታትሽንም ከአንቺ ያወርዳል፥ አዳራሾችሽም ይበዘበዛሉ።
12 ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እረኛ ከአንበሳ አፍ ሁለት እግርን ወይም የጆሮን ጫፍ እንደሚያድን፥ እንዲሁ በሰማርያ በአልጋ ማዕዘን፥ በደማስቆም በምንጣፍ ላይ የተቀመጡት የእስራኤል ልጆች ይድናሉ።
13 ፤ ስሙ፥ በያዕቆብም ቤት ላይ መስክሩ፥ ይላል የሠራዊት አምላክ ጌታ እግዚአብሔር።
14 ፤ እስራኤልን ስለ ኃጢአቱ በምበቀልበት ቀን የቤቴልን መሠዊያዎች ደግሞ እበቀላለሁ፤ የመሠዊያው ቀንዶች ይሰበራሉ፥ ወደ ምድርም ይወድቃሉ።
15 ፤ የክረምቱንና የበጋውን ቤት እመታለሁ፤ በዝሆንም ጥርስ የተለበጡት ቤቶች ይጠፋሉ፥ ታላላቆችም ቤቶች ይፈርሳሉ፥ ይላል እግዚአብሔር።